የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው

110

አርባ ምንጭ፤ግንቦት 15/2014/ኢዜአ/  የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ገለጸ ።

የፎረሙ ፕሬዚዳንት ተማሪ ጴጥሮስ ሀሩ እንደተናገረው ተማሪዎች የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ብቻ ለማሳካት ትኩረት እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

በዩኒቨርስቲው የ5ኛ ዓመት ኤሌክትሪክና ኮምፒዩተር ምህንድስና ተማሪና የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ፕሬዚዳንት ተማሪ ጴጥሮስ ሀሩ ስራችን መማር እስከሆነ ድረስ ከመጣንበት ዓላማ ውጭ ለሌላ አጀንዳ ተገዥ መሆን የለብንም" ሲል ለኢዜአ ተናግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ መሆን የቻለው እያንዳንዱ ተማሪ ሰላሙን ለማስጠበቅ ሃላፊነት በመውሰዱ መሆኑን ገልጿል።

ተማሪዎች ባህላቸውን እርስ በርስ በመለዋወጥ ሀገራዊ አንድነትን እንዲያጠናክሩ ፎረሙ በትኩረት ይሰራልም ብሏል።

ለመማር ማስተማር ሥራ ሰላማዊነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የዩኑቨርሲቲው የተለያየ ዓመት ተማሪዎች ገልጸዋል።

"ከተለያየ አካባቢ የራሳችንን ባህልና ቋንቋ ይዘን ወደ ዩኒቨርሲቲው ብንመጣም ተቋሙ ተቻችለንና ተከባብረን በጋራ የምንኖርበት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በድሩ ሂሪጎ በበኩላቸው፣ "የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ እንዲሆን የተማሪዎችን የተለያዩ አደረጃጀቶች ከአካባቢው ማህበረሰብና ፀጥታ አካላት ጋር በማስተሳሰር በቅንጅት እየተሰራ ነው” ብለዋል።


አደረጃጀቶቹን ተጠቅሞ በመነጋገር ችግሩ እየተፈቱ መሆኑን የገለጹት አቶ በድሩ፣ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲውን ስነ-ምግባርና ደንብ አክብረው እንዲማሩም ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተማሪዎች ትኩረታቸውን በትምህርትና ምርምር ላይ ከማድረግ ባለፈ አብሮነታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩም ጥሪ አቅርበዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባሉት ስድስት ካምፓሶች በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሐግብሮች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም