ስነ-ቃሎችን ለአገራዊ መግባባት ልንጠቀማቸውና ለትውልድ ልናስተላልፋቸው ይገባል - ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

264

አርባምንጭ ግንቦት 14/2014 (ኢዜአ) ... ስነ-ቃሎችን ለአገራዊ መግባባት ልንጠቀማቸውና ለትውልድ ልናስተላልፋቸው ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ተናገሩ፡፡

2ኛው አገር አቀፍ የስነ-ቃል ጉባኤ "ስነ ቃል ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መርህ ሐሳብ ትናንት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በመድረኩ እንዳሉት ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህልና ቋንቋ ባለቤት እንዲሁም የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ አገራዊ መግባባትን ለማስፈን የሚያስችሉ አገር በቀል ዕውቀቶች አሏት፡፡

እነዚህን የስነ-ቃል ሀብቶች ለአገር ግንባታ በሚጠቅም መልኩ ለትውልድ ለማስተላለፍ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ መሰነድና በስርዓተ ትምህርቱ ማካተት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተግባራዊነቱም ሚኒስቴሩ ከተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየሠራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም  ግጭትን የሚፈቱና ለአብሮነታችንና ለአንድነታችን በጎ ሚና ያላቸዉ የስነ-ቃል ሀብቶች በዚህ ረገድ ትኩረት ያገኙ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

በሚኒስቴሩ የባህልና ቋንቋዎች ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸዉ ለአገራዊ መግባባት አዎንታዊ ሚና ያላቸዉ ስነ-ቃሎች በተለያዩ ቋንቋዎች ተሰንደዉ ለትዉልድ እንዲተላለፉ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስነ-ቃል ሀብቶቻችን እንዳይሞቱና እንዳይጠፉ ልንንከባከባቸውና በአግባቡ ልንይዛቸዉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የብሔር ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች ብዛት "ከ80 በላይ ነው" ከማለት ውጭ በውል አይታወቅም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ አበክሮ እንደሚሠራ ነው ያረጋገጡት፡፡

"ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ጫፍ የረገጠ ብሔር ተኮር የፖለቲካ አተያዮች አገሪቱን እየተፈታተኗት ይገኛሉ" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለማየሁ ጩፋሞ ናቸው፡፡

አዲሱ ትውልድም ከአገር በቀል ዕውቀት ይልቅ ለመጤ ባህል የተጋለጠ በመሆኑ ለአገራዊ ስልቶች ባይተዋር አድርጎታል ያሉት ዶክተር አለማየሁ፤ የዘርፉ አካላት ምርምር በማድረግና በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማስገባት ትውልዱንና አገሩን ማዳን ተገቢ ይሆናል ነው ያሉት።

ስነ-ቃል ለአገራዊ መግባባት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ለአገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት በመስጠትና በመጠቀም ባህልን ጠብቆ ማቆየት ይገባል ያሉት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ቃል መምህር ዶክተር ለማ ንጋቱ ናቸዉ፡፡

በአገራችን የሚገኙ በርካታ ስነ-ቃሎች ተወራራሽ እንደመሆናቸው መጠን ማህበረሰቡ የጋራ በሆኑ እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአገራዊ መግባባት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

“ስነ-ቃል ለአገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ በተደረገው አገር አቀፍ ጉባኤ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ተመክሮባቸዋል።

በጉባዔው በፌዴራል፣ በክልሎችና በዞኖች የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዘርፉ ተጠሪዎች፣ ምሁራንና የጋሞ አባቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም