ለአገልግሎት ክፍያ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዳችን አነስተኛ ነው - የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች

63
አምቦ ግንቦት 10/2010  ለሸመቱት ዕቃና ለአገልግሎት ክፍያ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዳቸው አነስተኛ መሆኑን በምእራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ገለፀ ። የሽያጭ ደረሰኝ በማይቆርጡ  ሶስት የንግድ ድርጅቶች እያንዳንዳቸው  50 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉን የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን አስታውቋል። የጊምቢ ከተማ ነዋሪ አቶ አሸብር ብሩ በሰጡት አስተያየት  ሆቴል ገብተው ምግብም ሆነ መጠጥ ከተጠቀሙ በኋላ ለሚከፍሉት ገንዘብ አንድም ቀን ደረሰኝ ጠይቀው አያውቁም። አልፎ አልፎ አስተናጋጆች ደረሰኝ ቢያቀርቡላቸው እንኳን ጥለውት ይሄዳሉ እንጂ ትኩረት ሰጥተው አንብበውት እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡ አቶ ተመስገን ታፈሰ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በግዥ ወቅትም ሆነ  በአገልግሎት አሰጣጠጥ ሒደት ውስጥ ለሚከፍሉት ሂሳብ  ደረሰኝ ጠይቀው እንደማያውቁ ተናግረዋል። ነጋዴዎችም  ቢሆኑ  አልፎ አልፎ ደረሰኝ የሚሰጡት በአካባቢው አዲስና ከማያውቁት ሰው ጋር ሲገበያዩ ''ሊያጋልጠን ይችላል'' የሚል ስጋት ሲያድርባቸው ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል ። ለፈጸመው ግዥም ሆነ ለተጠቀመበት አገልግሎት የክፍያ  ደረሰኝ ሲጠይቅ በዋጋው ላይ  15 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ ስለሚጠየቅ በአብዛኛው ደረሰኝ እንደማይጠይቅ የገለፀው ደግሞ ወጣት ፈይሳ ሰለሞን ነው፡፡ አንዳንድ የንግድ ድርጅቶችም  ደንበኛቸው ደረሰኝ የሚፈልግ መሆኑን አስቀድመው ካወቁ ምርት ወይም አገልግሎት እያለ 'የለም' የሚሉበት ሁኔታ መታዘቡን አስታውቋል። ተጨማሪ እሴት ታክስ በአግባቡ አለመሰብሰብ በመንግስት ገቢ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን የተናገሩት ደግሞ የምእራብ ወለጋ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት የገቢ ኦፕሬሽን ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ክፍሉ ዋቅ ቶላ ናቸው ። ደረሰኝን ያለመቁረጥ ወንጀል መሆኑን የገለፁት የስራ ሒደት ባለቤቱ ህብረተሰቡ ራሱ የሚከፍለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመልሶ ለራሱ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ አገልግሎት የሚውል በመሆኑ ደረሰኝ ተከታትሎ መቀበል እንዳለበት አሳስበዋል ። የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ 12 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም በተጠቀሱት ምክንያቶች በእስካሁኑ ሂደት መሰብሰብ የተቻለው 10 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ክፍሉ ገለፃ ደረሰኝ በማይቆርጡ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ደረሰኝ እንደማይቆርጡ በተደረሰባቸው ሶስት የንግድ ተቋማት ላይ ክስ ተመስርቶ እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ተናግረዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የተጨማሪ እሴት ታክስን አስመልክቶ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም