በሃሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

163

ግንቦት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)በሃሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሚደረግ ጥረት ቦታ የለውም ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫው አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ትክክለኛ ማንነቱን የአለም ህዘብ እየተመለከተው መምጣቱንና በሃሰት ፕሮፖጋንዳ አሰልፎት የነበረው ድጋፍም መቀዛቀዙን ተከትሎ የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ልብ እገዛበታለሁ ያለውን የምርኮኞችን መፈታት አጀንዳ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

የወራሪነት፤ የአጥፊነትና የሃገር አፍራሽ ትክክለኛ ገጽታውን ለመሸፈንና ሰላም ፈላጊ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው መፍጨርጨር አንዱ መገለጫ ይህ ምርኮኞችን ለቀቅኩ የሚለው የሃሰት ትርክቱ ነው።

የሽብር ቡድኑ የአለምአቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር ከዚህም በፊት የሃሰት መረጃዎችን በማቀነባበርና ተባባሪ ሃይሎችን እያሰለፈ የሴራው አካል ሲያደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የህወሃት የሽብር ቡድን የአማራና አፋር አካባቢዎችን በሃይል ወረራ ስር አድርጎ በቆየባቸው ወቅቶች በግዳጅ ይዞ ኢሰብአዊ ተግባራትን ሲፈጽምባቸው የነበሩ ሰዎችንና ለራሱ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ምርኮኛ በማለት የሃገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማጭበርበር እየሞከረ ነው።

መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ እያደረገ ባለው ማጣራት በሽብር ቡድኑ ምርኮኞች ናቸው ተብለው የተለቀቁት አብዛኞቹ ዜጎች የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ በወጣበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ታግተው የቀሩ የሰራዊቱ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ከልዩ ልዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ለስራ ትግራይ ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲቪል ነዋሪዎችን አግቶ የቆየው የሽብር ቡድኑ፤ አሁን የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ባለው የፕሮፖጋንዳ ድራማ የመከላከያንና የተለያዩ ጸጥታ ሃይሎችን መለዮ በማልበስ በምርኮኛ ስም አሰልፏቸዋል።

የህወሃት ሽብር ቡድን ከሰሞኑ የጦርነት ክተት እያወጀና በይፋም እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን ተከትሎ ያለችውን እንጥፍጣፊ ስንቅ ወደ ጦርነት ለማዞርና ለዳግም ጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ለመሆኑ የአሁኑ ድርጊቱ ሁነኛ ማሳያ ነው።

የዚህ እኩይ ሽብር ቡድን ተባባሪ የሆኑና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔና ሌሎችም ታጣቂ ጽንፈኛ ቡድኖች የዚህ ፕሮፖጋንዳ ተባባሪዎች ናቸው።

የህወሃት የሽብር ቡድን ከእነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች አባላትን በመመልመልና በማሰባሰብ ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ሰርጎ ገብ ሃይሎችንም በምርኮኛ ስም አደራጅቶ የእኩይ ተልእኮው ማስፈጸሚያና መረጃ መቀበያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመንግስት በኩል የተደረገው ማጣራት አመልክቷል።

መላው ህዝብም ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ የሚነዙትን ሃሰተኛ ወሬዎች አላማና የህወሃትን የአጥፊነት ተልዕኮ በማስታወስ አሁንም የሚያሰራጫቸው ወሬዎች የጥፋት ተልእኮውን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም