የኢትዮጵያ የበዓል አከባበርና የብሄር ብሄረሰቦች አዝናኝ ውዝዋዜ ጎብኝዎችን የመሳብ አቅም አለው-ዲፕሎማቶች

127
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 የኢትዮጵያ የበዓል አከባበርና የብሄር ብሄረሰቦች ውዝዋዜ ጎብኝዎችን የመሳብ አቅም እንዳለው ዲፕሎማቶች ገለጹ። ኢትዮጵያ  ሊጎበኙ ከሚገባቸውና የሰውን ልጅ ቀልብ የሚስቡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦች ያላት አገር ናት። በተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች ደምቀው የሚከበሩት ኃይማኖታዊና ብሄራዊ በዓላት የተለያዩ የዓለም ህዝቦችን ቀልብ የመሳብ አቅም እንዳላቸው ነው በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች የሚገልጹት። በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ጉስታቮ ግሪፖ ለኢዜአ እንዳሉት፤ "የኢትዮጵያ ብሄራዊ በዓል አከባበር የጎብኝዎችን ቀልብ መሳብ የሚችል ነው"። የኢትዮጵያ ማራኪ መስህቦች ከአርጀንቲና ጋር ያለውን የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ግንኙነት የበለጠ ማጎልበት የሚያስችልም ነው ብለዋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ በዓል ላይ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የቱሪዝም ፍሰት ማሻሻል እንችላለን፤ በእርግጥ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአርጀንቲና በተመሳሳይ በርካታ አርጀንቲናውያን በኢትዮጵያ ጉብኝት ስለሚያደርጉ ተመጣጣኝ የሆነ ግንኙነት አለን።” በአፍሪካ ህብረት የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፉሚዮ ሽሚዙ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ያላት አገር መሆኗን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኃይማኖታዊና ብሄራዊ በዓላትን ከኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ጋር ማሳለፍ በመቻሌም ኩራት ይሰማኛል ብለዋል። ረጅም እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነቱና ሳቢነቱ ባለበት እንዲቀጥል ሀገራዊ ይዘቱን ጠብቆ መሄድ እንዳለበት ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክና የባህል እሴት ያላት አገር ናት፣ ይህ ማራኪ ባህል ተጠብቆ መቆየት አለበት፤ በዚህች አገር በመገኘቴና ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ ህዝብ ጋር በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”   የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው መንግስት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም የገቢ ማስገኛ ዘርፍ ሆኖ ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የውጭ ዜጎችም ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት በመሆኗ ማራኪ የሆኑ የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘት የጋራ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል። “ለሁሉም የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ አባላት ማስተላለፍ የምፈልገው ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት ምቹ የቱሪዝም መንደር ናት፤ በመሆኑም ሁሉም አምባሳደሮች ኢንቨስተሮቻችሁ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ እንዲሁም በመጎብኘት የጋራ ተጠቃሚ እንድንሆን በጋራ መስራት አለብን።” የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ “አንድ ሆነን አንድ እንበል” በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ተከብሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም