የኢትዮጵያን ህልውና በአስተማማኝ መልኩ የሚያስጠብቅ ሰራዊት መገንባታችንን ባንዳዎችና ጠላቶቻችን ሊያውቁት ይገባል

171

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና በአስተማማኝ መልኩ የሚያስጠብቅ የአገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱን ጠላቶቻችንና ባንዳዎች ሊያውቁት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

በ2012 ዓ.ም ስራ የጀመረው የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በደህንነትና ስትራቴጂ ጥናት ያሰጠለናቸውን የኢትዮጵያና የጎረቤት ሀገራት ወታደራዊ መኮንኖችና ሌሎች የደህንነት አመራሮችን አስመርቋል።

በምርቃቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ ለተመራቂዎቹ የመከላከያ የክብር ባጅና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል።

በመልእክታቸውም ኢትዮጵያ ከ100 ዓመት የተሻገረና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የመከላከያ ተቋም እንዳላት በመጥቀስ ተቋሙ ራሱን እያዘመነ ኢትዮጵያን የሚመጥን እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"የሀገር መከላከያ የመጀመሪያ ተልዕኮው ኢትዮጵያን ማስቀጠል ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በርካታ ችግሮች ስላጋጠሙት ራሱን ለማስቀጠል ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፍሉን ተናግረዋል።

ተቋሙ እንደ ሀገር ያለፈውን አንድ ዓመት ጦርነትን ጨምሮ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም አጋጣሚዎችን እንደ እድል በመውሰድ ከፍ ወዳለ ምእራፍ ተሸጋግሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ወድዶ ሉዓላዊነቷን የሚያስከብር ሰራዊት በመገንባት ሂደትም የመከላከያ ዋር ኮሌጅ የጀመረው የደህንነትና ስትራቴጂ ትምህርት ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ከብሔርና የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆኑን በማንሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ከዛሬ  ተመራቂዎች ብዙ ይጠብቃሉ ብለዋል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ፤ የዛሬ ተመራቂዎች የደህንነት ስጋቶችን በአግባቡ በመተንተን የኢትዮጵያንና የጎረቤት ሀገራትን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል እወቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በትምህርት ቆይታቸውም አካባቢያዊና ሀገራዊ የደህነነት ምህዳርን ተረድተው በውስን ሀብት ግጭቶችን በዘመናዊ መንገድ መፍታትና መከላከል የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የኢትዮጵያ የህልውና ስጋት በሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጥረት ተወግዶ በአስተማማኝ ቁመና ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

መከላከያ ሰራዊት ካለበት የግዳጅ ስምሪት በተጓዳኝ የሀገርን ሰላምና ህልውናን በዘላቂነት ለማስከበር ብቃቱና ዝግጁነቱን የሚያሳድጉ ስልጠና እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዘመኑ የሚጠይቀውን ስልጠና የብቃት ደረጃ ለማደራጀት አስፈላጊ ግብአት እንዲሟላላቸው ይሰራል ብለዋል።

"የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ብሔርም ሆነ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የለውም፤ በህይወታቸው ዋጋ ከፍለው ኢትዮጵያን ከነክብሯ የሚያስቀጥሉ ጀግኖች ናቸው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመልእክታቸው።

የኢትዮጵያን ህልውና በአስተማማኝ መልኩ የሚያስጠብቅ ሰራዊት መገንባታችንን ባንዳዎችና ጠላቶቻችን ሊያውቁት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።አዲ

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሞክሩ ባንዳዎች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ትምህርት የሚሰጥ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም