ከአገር ውድመት ባለፈ በሰዎች አካልና አእምሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትለው የጦርነት አዙሪት መውጣት ይገባል

385

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአገር ውድመት ባለፈ በሰዎች አካልና አእምሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትለው የጦርነት አዙሪት በመውጣት ምክክርን የመፈትሄ አማራጭ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማሕበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ጦርነት ፈፅሞ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ብለዋል።

'በጦርነት የሚገኝ መፍትሄና የሚመጣ ሰላምም' አይኖርም ያሉት  ዋና ዳይሬክተሩ መነጋገር፣ በመመካከር፣ በሃሳብ የበላይነት መሸናነፍ ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።

የጦርነት መዘዙ አገርን ማውደም ህዝብን ለችግር መዳረግ በተለይም ደግሞ ህፃናት፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ለከፋ ስቃይና እንግልት የሚዳርግ የብዙ ውስብስብ ችግሮች መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የኢትዮጵያ መስማት የተሳናችው ብሔራዊ ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጳውሎስ ካሱ፤ በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን ጦርነት አማራጭ ከሆነ አገርና ህዝብን በእጅጉ መጉዳቱ የማይቀር መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከልና ሲከሰትም በምክክርና መግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለአገር ሰላምና ለህዝብ ደህንነት  ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ይመክራሉ።

በርካታ አምራች ዜጎችአካላቸውን የሚያጡት በጦርነት ጊዜ መሆኑን ገልጸው የጦርነት አማራጭ  አገርን ወደ ብልጽግና ለመውሰድ የሚደረገውን  ጥረት የሚያደናቅፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ የዘላቂ ሰላም መፍትሄ እንደሚያመጣ የታመነበት አገራዊ የምክክር መድረክ ጥሩ መንገድ የሚመራ ስለመሆኑንም ገልጸዋል።

የመመካከር፣ የመነጋገር፣ የአብሮነትና ትብብር ውጤቱ ከአገርም የሚሻገር ትርጉም ያለው በመሆኑ ሁላችንም ለዚሁ መልካም ተግባር እንዘጋጅ በማለት መልእክታቸውን አስተላልገፈዋለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም