የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት 1 ሺህ መጻሕፍት አስረከበ

192

ግንቦት 12/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በየክፍለ-ከተማ ከሚገኙ ወጣቶች ያሰባሰበውን 1 ሺ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረክቧል።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት  "ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር የሚቆየውን የመጻህፍት ማሰባሰብ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንን ተከትሎ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጥበቡ በቀለ የተሰበሰበውን መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት የበላይ ተጠሪ ለአቶ ውባየሁ ማሞ አስረክበዋል።  

ቢሮው ያስረከባቸው መጻሀፍት የተለያየ ይዘት ያላቸውና ትውልድን የሚቀርጹ መሆናቸው ተገልጿል።

የቤተ-መጻሕፍቱ የበላይ ተጠሪ አቶ ውባየሁ ማሞ በበኩላቸው፤ በተማረ ሃይል የተገነባች አገር ለመፍጠር አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ይህንንም ግብ እውን ለማድረግ ለሚሰራው አብርሆት መጻሕፍት መለገስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እውቀትን መሰረት ያደረገ ትውልድ በመገንባት የተሻለ ሀገር ተረካቢ ኃይል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የመጻህፍት የማሰባሰብ ሥራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቤተ-መጻሕፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት የመያዝ አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም