የአፍላ ወጣቶች፣ የእናቶች አመጋገብ ሥርዓትና የቅድመ-ወሊድ አገልግሎት ውጤታማ ሆኗል

268

 ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የአላይቭ ኤንድ ትራይቭ ኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት በደቡብና በሶማሌ ክልል ተግባራዊ ያደረገው የአፍላ ወጣቶች፣ የእናቶች አመጋገብ ሥርዓትና የቅድመ-ወሊድ አገልግሎት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ።

የአላይቭ ኤንድ ትራይቭ ኢትዮጵያ የአፍላ ወጣቶች፣ የእናቶች አመጋገብ ሥርዓትና የቅድመ-ወሊድ አገልግሎት መርኃ-ግብር በደቡብና በሶማሌ ክልል በተመረጡ ሰባት ወረዳዎች ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ገቢራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።

መርኃ-ግብሩ በዋናነት ከአምስቱ የምግብ ምድቦች በየቀኑ መመገብ፣ በበቂ መጠንና ድግግሞሽ በየቀኑ መመገብ፣ በአይረንና የፎሌት እንክብልን በየቀኑ መውሰድ፣ የሰውነት ክብደት መጨመርን መከታተል፣ ስለ ጡት ማጥባት እንዲሁም ንጽህናን መጠበቅ የተመለከቱ መረጃዎች አቅርቧል።

አላይቭ ኤንድ ትራይቭ ኢትዮጵያ ከቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያካሄደው ይኸው መርኃ-ግብር 1 ሺህ 500 የሚጠጉ አፍላ ወጣቶችና ቤተሰቦችን ተጠቃሚ አድርጓል ተብሏል።

ተቋሙ የመርኃ-ግብሩን ውጤታማነት ለመገምገም ላለፉት ሦስት ወራት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መርኃ- ግብሩ አዋጭ መሆናቸውን የአላይቭ ኤንድ ትራይቭ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልአዚዝ ዓሊ ተናግረዋል።  

በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት በፊት ቁርስ በመደበኛነት የመብላትና በትምህርት ቤት ዕረፍት ወቅት ጤናማ መክሰስ የማግኘት አዲስ የአመጋገብ ልምዶችን እንዲከተሉ ረድቷቸዋልም ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የአፍላ ወጣቶች፣ የእናቶች አመጋገብ ሥርዓትና የቅድመ-ወሊድ አገልግሎት አሁን ላይ በኦሮሚያ፣ አማራና አፋር ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ መርኃ-ግብሩን እያስተዋወቀ መሆኑንም ዶክተር አብዱልአዚዝ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት በሕጻናትና እናቶች ላይ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላይ ጉልህ ቅነሳ አሳይታለች።

ዶክተር መሠረት አያይዘውም በሁሉም የህይወት እርከኖች ውስጥ የተመጣጠነ ምግብን ማረጋገጥ ረዥም ዕድሜንና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

የመንግሥት የአሥር ዓመታት የወደፊት እቅድ ከአምስት ዓመት በታች የሕጻናት ሞትን በ13 ከመቶ ለመቀነስ አጽንኦት መስጠቱንና በሰቆጣ ዲክላሬሽን የሕጻናትን የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማጥፋት ቃል መግባቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም