ባለፉት አሥር ወራት 82 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው እቃዎች ከቀረጥ ነጻ ገብተዋል

111

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት አሥር ወራት 82 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው እቃዎች ከቀረጥ ነጻ መግባታቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።

የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፤ የተቋሙን የአሥር ወራት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም ባለፉት አሥር ወራት ከቀረጥ ነጻ መብትን በመጠቀም 82 ቢሊየን ብር ከቀረጥ ነጻ እቃዎች ከውጭ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከቀረጥ ነጻ ደብዳቤ ሲጻፍ በትክክል ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ያለበትን ድርጅት ከአገርና ሕዝብ ጠቀሜታ አንጻር ማጤን ይገባል ብለዋል።

እቃዎች ከቀረጥ ነጻ ከገቡ በኋላም ለተፈለገው ዓላማ መዋላቸውን መከታተልና መቆጣጠር ይገባል ነው ያሉት።

ቀደም ሲል በየክልሎችና መሥሪያ ቤቱ ይሰጥ የነበረው የቀረጥ ነጻ መብት በአሁኑ ወቅት በአንድ ማዕከል በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል መደረጉን አውስተው ጥያቄዎችን በጥንቃቄ ማየት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፤ የቀረጥና ታክስ ነጻ መብት በልዩ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት አሥር ወራት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግስት 38 ቢሊየን ብር ከቀረጥ ነጻ መፍቀዱን ጠቁመዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድን የመከላከል አቅም እየጨመረ ቢመጣም የወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እንቅስቃሴ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ከመጠቀም ጀምሮ የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች እንዲሁም አደረጃጀታቸው ቀደም ሲል ከነበረው እየጠነከረ መምጣቱንም ነው የገለጹት።

በመሆኑም ከዘመኑ ጋር የሚመጥን የቴክኖሎጂ አሰራርን በመጠቀም ችግሩን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮንትሮባንድ ንግድ አገርና ሕዝብን በመጉዳት በአቋራጭ ለመክበር የሚጥሩ ህገ-ወጦችን በመከላከል ረገድ የሁሉም ጥረት እንዲታከል ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም