በመዲናው የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው ሥፍራዎች የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን የማጽዳትና የመጠገን ሥራ እየተሰራ ነው

85

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው ሥፍራዎች የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን የማጽዳትና የመጠገን ሥራ እየተሰራ መሆኑን የመዲናዋ የመንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።


የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን እንደገለጹት፤ መጪው የክረምት ወቅት ከባድ ዝናብ እንደሚኖር የሚቲዎሮሎጅ ትንበያ ያመለክታል።


ይህንንም ተከትሎ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን በለያቸው ሥፍራዎች የሚገኙ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን የማጽዳትና የመጠገን ሥራ እየተሰራ ነው።


ከመንገድ ግንባታና ጥገና በተጨማሪ ተቋሙ ጽዳትና ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ ‘የፍሳሽ መስመር ጽዳትና ጥገና መደረጉን ነው የገለጹት።


ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ለጽዳት ተብሎ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ክዳኖች በሚከፈቱበት ወቅት ደረቅ ቆሻሻዎችን በማስወገድ መስመሮች እንዲዘጉ በማድረግ ችግሩን ማባባሱን ገልጸዋል።


ደረቅ ቆሻሻ በፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች የሚጥሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ድርጊት በመቆጠብ አካባቢያቸውን በኃላፊነት ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።


እስካሁን 42 ቦታዎች ላይ ጥገናና ጽዳት እየተደረገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ እነዚህን ቦታዎች ህገ-ወጥ ተግባራት ከሚፈጽሙ ሰዎች እንዲከላከል ጠይቀዋል።


የመንገድ ኃብት የጋራ ኃብት በመሆኑ ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በተዘረጋለት መሰረት በመተግበር አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።


በአዲስ አበባ በሳምንት ሁለት ቀን ቤት ለቤት ቆሻሻ የሚሰበስቡ ማኅበራት እንዳሉት ጠቁመዋል።


በመዲናዋ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በዘመነበት በዚህ ወቅት ኅብረተሰቡ ሥርዓቱን ተከትሎ ቆሻሻ ሊያስወግድ ይገባል ያሉት ደግሞ የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ናቸው።


የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ባህል እየተሻሻለ ቢመጣም ሁሉም ኅብረተሰብ ባለቤት ሆኖ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ባህል አሁንም በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉን ገልጸዋል።


መጪው ጊዜ የክረምት በመሆኑ አካባቢን በማጽዳት ዘመቻ በመሳተፍ አካባቢውን ከሥጋት ሊታደግ ይገባል ብለዋል።


ሁሉም ዜጋ አካባቢውን ከጎርፍ አደጋ ከሥጋት ነጻ የማድረግ የሁሉም ኅብረተሰብ ግዴታ በመሆኑ ሁሉም አካባቢውን በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️