የከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የቤት ችግርን ለመፍታት እየሰራ ነው

130

ደብረ ማርቆስ ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ) የደብር ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን ተድላ ለኢዜአ እንዳሉት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው።

አስተዳደሩ ካለፈው ህዳር ወር 2014 ዓ/ም ጀምሮ ህብረተሰቡን በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት በማሳተፍ ችግሩን ለማቃለል ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

በህብረተሰቡና በመንግስት ቅንጅት በተደረገው ጥረት 59 የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎቹ እየተላለፉ መሆኑን ጠቅሰው 14 ቤቶች ደግሞ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለመኖሪያ ቤቶቹ ግንብታ ህብረተሰቡ 3 ሚሊየን በጥሪ ገንዘብና ፣ ከ5 ሚሊየን 700 ሺህ ብር በላይ በቁሳቁስ ፣ ከ300 ሺህ ብር የሚገመት በጉልበት ድጋፈ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶቹ ግንባታ በሊዝ መነሻ ዋጋ ከ9 መቶ 78 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ 3 ሺህ 915 ካሬ ሜትር ቦታ መስጠቱንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ወራት ተጨማሪ የአዳዲስ ቤት ግንባታና የቀበሌ ቤቶችን በማደስ  ለአቅም  ደካማ ይህብረተሰብ  ክፍሎች የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የቀን ስራ ሰርተው ከሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ለቤት ኪራይ በመክፈል ለችግር ተዳርግው እንደነበር የተናገሩት በከተማው የቀበሌ 07 ነዋሪ ወይዘሮ ውዴ ጥበቡ  አሁን ላይ መንግስትና ህብረተሰቡ ባደረጉት ጥረት ከመኖሪያ ቤት ችግር መላቀቃቸውን ገልፀዋል።

''አሁን ላይ ባለ ሁለት ክፍል ቤት የተሰጠኝ በመሆኑ ልጆቼን በአግባቡ እንዳሳድግ በማድረፍና በወር ለቤት ኪራይ እከፍለው የነበረውን ሰባት መቶ ብር ለኑሮዬ መደጎሚያ ማዋል ችያለሁ'' ሲሉ ተናግረዋል።

''ቀደም ሲል እኖርበት የነበረው አነስተኛ ክፍል በንፋስ በመውደቁ ከልጆቼ ጋር ችግር ውስጥ ቆይቻለሁ'' የሚሉት ደግሞ የቀበሌ 05 ነዋሪ ወይዘሮ የሽወርቅ ወንዴ ናቸው።

አሁን ላይ ስራ ጭምር ሰርቼ መጠቀም የሚያስችል ቤት በህብረተሰቡና በመንግስት ትብብር እየተገነባልኝ በመሆኑ ተደስቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ማህብረሰቡ ተሳትፎ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች ከ50 በላይ ቤቶችን አድሶና ገንብቶ ማስርከቡን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም