ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን በመጠቀም የሕወሓትን አላማ ማስፈጸማቸውን እንዲያቆሙ ተጠየቀ

147

ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን በመጠቀም የሕወሓትን አላማ ለማስፈጸም የሚያከናውኑትን ተግባር እንዲያቆሙ ዘጠኝ ተቋማት ለዳይሬክተሩ በጋራ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ።

ደብዳቤውን የጻፉት የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር፣ ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ)፣ ’ኢትዮጵያን ዳያስፖራ ሃይ ሌቭል አድቫይዘሪ ካውንስል ኦን ኮቪድ-19’፣ ’ኢትዮጵያን ስኮላርስ ኢን ኖርዲክ ካንትሪስ’፣ የደቡብ አፍሪካ የሕክምና ማህበር፣ የሌሴቶ ሕክምና ማህበር እና ‘ፒፕል ቱ ፒፕል’ የተሰኙ ተቋማት ናቸው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለፈው 18 ወር በነበረው ግጭት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ፖለቲካዊና ግልጽ ወገንተኝነት ያለው አካሄድን መከተላቸውን ተቋማቱ ገልጸዋል።

በንግግርና በድርጊታቸውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተና የተዛባ አቋም እንዲይዙ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ በሚጽፏቸው ጽሁፎችና በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ድርጊትና በሕዝብ ላይ ባደረሰው መከራ ላይ ዝምታን መርጠዋል ብለዋል።

ሕወሓት በፈጸመው ወረራ በርካታ የጤና ተቋማትን ማውደሙንና መዝረፉን አስታውሰው፤ ቡድኑ ንጹሃንን በመግደልና አስገድዶ በመድፈር ወንጀሎችን መፈጸሙን አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ሕወሓት በክልሎቹ የፈጸመውን ድርጊት በሚያወጡት ሪፖርት እየገለጹ በሚገኙበት ወቅት ዶክተር ቴድሮስ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር አለመኖር አድሎአዊነታቸው ለአንድ አካል የሚያሳይ እንደሆነ ነው ተቋማቱ በደብዳቤው ላይ የገለጹት።

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚቀርብላቸው ጥሪ ምላሽ አለመስጠታቸው የሚያሳዝን ተግባር ነው ብለዋል።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እያደናቀፈ እንደሚገኝ የጠቀሰው ግልጽ ደብዳቤው፤ ዶክተር ቴድሮስ በአሜሪካ በነበራቸው ጉብኝት ከባለስልጣናትና ከሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት አላማው በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለመጎትጎት እንደሆነ ጠቅሰዋል።ጉብኝቱ የ’ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ሕጎች እንዲጸድቁ ግፊት ለማድረግ መሆኑን እንረዳለን ነው ያሉት ተቋማቱ።

ዶክተር ቴድሮስ የዓለምን ሕዝብ ጤና ለመጠበቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሕወሓትን አላማ ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ነው፤ ከዚህም ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል።አፍራሽ የፖለቲካ እንቅስቃሴና የዘር ውግንናቸውን በመተው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጤና መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ተቋማቱ ጠይቀዋል።

ዘጠኙ ተቋማት በአማራና አፋር ክልሎች በሕወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋምና ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሥነ ምግባር ጥሰት እንዲጠየቁ በጥር ወር 2014 ዓ.ም ለድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ቦርድ የቅሬታ ማመልከቻ ማስገባቱ ይታወሳል።

በማመልከቻው ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በዋና ዳይሬክተሩ ላይ የሕግ እና የሙያዊ ሥነ ምግባር እንዲሁም የሞራል ጥያቄዎች እንዳሉት ገልጿል።

ዶክተር ቴድሮስ ለአንድ ወገን የያዙት አድሏዊ አቋም ከፍተኛ ኃላፊነት በያዙበት ቦታ ያላቸውን ሙያዊ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው በማመልከቻው ላይ ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን ቅሬታ አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም