በኢትዮጵያ በአካባቢና ደን ህግ ማስከበር ሙያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ተመረቁ

142
ሰንዳፋ  ጳጉሜን  3/2010 የአከባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ስልጠና ያገኙ የአከባቢና ደን ህግ ማስከበር 42 ባለሙያዎች ዛሬ ተመረቁ። በኢትዮጵያ በአከባቢና ደን ህግ ማስከበር ሙያ ባለሙያዎች ሲሰለጥኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። የባለሙያዎቹ የምርቃት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ሰንዳፋ በሚገኘው የኮሌጁ መኮንኖች ክበብ ተካሂዷል። ሰልጣኞቹ በሚኒስቴሩ ሥር ያሉ የክልል ባለሙያዎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ናቸው። ሰልጣኞቹ ህገ-መንግስቱን፣ የወንጀል ህጉን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ህጎች ላይ ትምህርት የተሰጣቸው ሲሆን በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያስችል ስልጠናም ተከታትለዋል። ከዚህም ሌላ በወንጀል መረጃ ትንተና፣ በወንጀል ስፍራዎች አጠባበቅ፣ በፎሬንሲክ ማስረጃ አሰባሰብና አያያዝ፣ አላላክና የምርመራ መዝገብ አደረጃጀት ሪፖርት አጻጻፍ ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በኮሌጁ የአጫጫር ስልጠናዎች ዲፓርትመንት ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ተገኝ እንዳሉት፣ ባለሙያዎች ከደንና አካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች የላቀ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት እንዲከታተሉ ተደርጓል። በቀጣይም ኮሌጁ በረጃጅምም ሆነ በአጫጭር ስልጠና መርሃ ግብሮች ከሚኒስቴሩ ጋር የሚያደርገውን ትብብር እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል። የኮሌጁ ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጋሹ ዓለማየሁ ስልጠናው በዘርፉ ያለውን የህግ ጥሰት ለመከላከልና ከፖሊስ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። በሚኒስቴሩ ኃብት ማፈላለግና ፕሮጀክቶች ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወርዲ ሀሺም በበኩላቸው የደንና አካባቢ ወንጀል ጥሰቶችን ለመከላከል ህጎች ቢወጡም ተግባራዊነቱ ላይ ሰፊ ክፍተቶች የሚታይ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ በመስኩ የህጉ አተገባበር ላይ በቂ ግንዛቤ አለመኖር መሆኑን ገልጸው ክፍተቱን ለመሙላት መሰል ስልጠናዎች ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት። ተመራቂዎች በበኩላቸው በቀጣይ ለሚሰሩት ስራ ስልጠናው አጋዥ እንደሚሆንላቸው   ገልጸዋል። ተመራቂ ወይዘሮ መድሃኒት አሰፋ እንዳለችው  በስልጠናው  ወንጀሎች እንዴት እንደሚመረምሩ  የመረጃ አሰባሰብና ፣ የተጠናከረ መረጃ  ለህግ አካል ማቅረብ  ስለሚቻልበት   ዘዴም በስፋት ተምረዋል፡፡ ከፖሊስ ጋር  እንዴት በቅንጅት እንደምንሰራና  አስፈላጊውን የክህሎት ስልጠና   አግኝተን ስለወጣን  በቀጣይ የተሻለ ስራ እንሰራለን  ያለው ደግሞ  አቶ  ሙሉ ቀን ሞሲሳ  ነው፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም