ሀገር አቀፉ የባድሜንተን ሻምፒዮና በኦሮሚያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

101

ጅማ ፣ ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ)— በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የነበረው ሀገር አቀፉ የባድሜንተን ሻምፒዮና በኦሮሚያ ክልል አሸናፊነት ተጠናቋል።

በነጠላ እና ጥንድ በተደረገው ውድድር በሁሉም ዘርፍ ኦሮሚያ ክልል አንደኛ በመውጣት የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

የደቡብ ክልል ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

በውድድሩ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባድሜንተን ክለቦች ተሳትፈዋል።

በባድሜንተን ስፖርት ሻምፒዮናው ደራርቱ መኮንን እና ኦላና ባይሳ የውድድሩ ኮኮብ ተጫዋቾች ሆነው ተመርጠዋል።

በርካታ ክልሎች በሻምፒዮናው ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም በገንዘብና እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት አለመገኘታቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ እታለም ተሰማ ባስተላለፉት መልዕክት ጅማ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ እና የመላው አፍሪካ ባድሜንተን ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ መሰረተ ልማት ያሉት  መሆኑን ተናግረዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ሃላፊ አቶ አማኑ ኤባ “የባድሜንተን ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅና እንዲዘወተር ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው” ብለዋል።

 ይህንኑ ለማሳካት የስፖርት አካዳሚው በስፖርታዊ ቁሳቁስ፣ በሙያ እና ስልጠና ዝግጁነት እንዳለው  ተናግረዋል።