በአትክልትና ፍራፍሬ ሠርቶ ማሳያ ልማት ውጤታማ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

234

አዳማ ግንቦት 10/2014(ኢዜአ)...በምስራቅ ሸዋ ዞን በአትክልትና ፍራፍሬ በሠርቶ ማሳያ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ።

በዞኑ ተደራጅተው ሰርቶ ማሳያ  በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮች ማሳ የመስክ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ዛሬ ተካሄዷል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል የዱግዳ ወረዳ በቀለችሳ ግሪሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በቴ ሚደቅሶ እንደገለፁት በፓፓያ ሠርቶ ማሳያ ልማት ተሠማርተው ውጤታማ ሆነዋል።

በልማቱ ከምርጥ ዘር ጀምሮ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አጠቃቀም ላይ የባለሙያዎች የዕለት ተዕለት ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸው ተናግረዋል።

ለረዥም ጊዜ ቲማትም፣  ሽንኩርትና ፎሶሊያ በባህላዊ ዘዴ ሲያመርቱ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደር በቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሬቱ የሚሰጠው ምርት እየቀነሰ በመምጣቱ በአማራጭ ወደ ፓፓያ ልማት መግባታቸውን አንስተዋል።

በአምስት ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የፓፓያ ሠርቶ ማሳያ ልማት እያከናወኑ መሆኑን የገለፁት አርሶ አደር በቴ፤ በተለይም በፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎች እንዲሁም የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በባለሙያዎች እየታገዙ በመጠቀማቸው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ከዚህ ቀደም በቀርጥ ከ5 አሰከ 6ሺህ ብር ስናወጣ ነበር" ያሉት አርሶ አደር በቴ አሁን ላይ በቀርጥ አስከ 500 ብር ብቻ ወጪ በማድረግ ምርታቸውን በእጥፍ በማሳደግ  ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ሽጉጡ አላታ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሠርቶ ማሳያ ፕሮጀክት ታቅፈው ቃሪያ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ መታቀፋቸው በምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ  ውጤታማ ከመሆን አልፈው በየዕለቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂና ዕውቀት እየቀሰሙ መሆናቸውን ጠቁመው ለአካባቢው አርሶ አደሮችም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ልምዳቸውን እያካፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ ቃሪያ  በማልማት በቀን 30 ኩንታል ምርት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በግብርና ባለሙያዎች  እገዛና ድጋፍ  በ200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የቃሪያ፣ ጎመን፣ ፓፓያ ጨምሮ ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን  ማልማት የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተግባር ሙያዊ ዕገዛ ከማድረጋቸው ባለፈ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር፣ የፋብሪካ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎች አጠቃቀምና አቅርቦት ላይ ተከታታይ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን አመልክተዋል።

አሁን ላይ የተከሉት ቃሪያ እስከ ስድስት ዙር  ምርት የሚሰጥ በመሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አስታውቀዋል።

"ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩን በቡድን በማደራጀት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አላማ በማድረግ ተግባራዊ የተደረገ ነው " ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ናቸው።

በፕሮጀክቱ በዞኑ በስድስት ወረዳዎች ከ2 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች  ታቅፈው የአትክልትና ፍራፍሬ ሠርቶ ማሳያ ስራ እያከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

ለተሳታፊ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር፣ የፋብሪካ  ማዳበሪያና ሌሎች ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግሉ ግብዓቶች  በፕሮጀክቱ እየቀረቡ ከመሆኑም ባለፈ የሙያ እገዛና በየሳምንቱ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ሽግግር ላይ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እየተደረገ  መሆኑን ተናግረዋል።

ልማቱን ከአነስተኛ ማሳ ሰርቶ ማሳያ ወደ ማዕከል ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፕሮጄክቱ አስተባባሪ አቶ ቀኖ ረጋሳ በበኩላቸው በበሽታ የማይጠቁና ምርትና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆነ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ በአርሶ አደሩ ዘንድ የዕውቀት፣ የልምድና የቴክኖሎጂ ሽግግር በፍጥነት እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው  ገልጸዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የዞኑ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎችን እንዲሁም  ባላድርሻ አካላት  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም