የጥቂቶችን እኩይ ተግባር በማክሸፍ የብዙኃኑን የሰላም ፍላጎት ማስጠበቅ ይገባል - አቶ ብናልፍ አንዷለም

112

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ) የጥቂቶችን እኩይ ተግባር በጋራ ተከላክሎ በማክሸፍ የብዙኃኑን የሰላም ፍላጎት ማስጠበቅ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም አስገነዘቡ።

የሰላም ሚኒስቴር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በግጭት አዝማሚያዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ እየመከረ ነው ።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሰላም የሰው ልጅ ያለ ምንም የቋንቋ፣ የብሔርና ሃይማኖት ልዩነት ሊያጣቸው ከማይፈልጋቸው ነገሮች በግንባር ቀደም ደረጃ ላይ ይገኛል።

ጥቂቶች ለግል ጥቅምና ስልጣን የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር በጋራ በማክሸፍ የብዙኃኑን የሰላም ፍላጎት ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ስለ ሰላም ማንኛውንም ዋጋ መክፈል የሚችሉና በርካታ የሰላም እሴቶች ያላቸው ህዝቦች ባለቤት መሆኗን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

በሀገሪቱ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች በጥቂቶች ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው "ሰላም ወዳዱን ኢትዮጵያዊ በማንቃት ለሰላሙ ዘብ ሆኖ እንዲቆም መስራት አለብን" ሲሉም አስገንዝበዋል።

''እንደ ሀገር ህዝብን ይዘን ሰላም ላይ በመረባረብ የባንዳዎችን ጥፋት ከተከላከልን የሰላማችን ጉዳይ ፈተና ሆኖ አይቀጥልም'' ብለዋል።

በትንሽ ምክንያት ሳይታሰብ የመፈጠር ባህርይ ያለው ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አካባቢዎችን የሚያዳርስ በመሆኑ የሰላምን ጉዳይ በክልልና አካባቢ ባለመከፋፈል አንዱ የአንዱን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው "ሰላም ሲሰፍን ዜጎች ያላቸውን ዕውቀትና አቅም ለሀገር እድገትና ብልጽግና ያበረክታሉ" ብለዋል ።

ሰላምና የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ የመንግስት ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳሰበዋል።

የክልሉ ህዝቦች የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎች በለውጡ መንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ክልሉ እንደ አዲስነቱ የፀጥታ ችግሮች እንዳይገጥሙት የፌደራል መንግስት እያደረገ ላለው ድጋፍ ዶክተር ነጋሽ ምስጋና አቅርበዋል።

ክልሉ ለሰላምና ልማት ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

በግጭት አዝማሚያዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክረው ጉባኤ እንደቀጠለ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም