ቢሮው የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተፈራረመ

135

ሚዛን አማን፣  ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንን አቅም ማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱ 1 ሺህ 52 ለሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የድህረ ምረቃ ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንዳሉት ስምምነቱ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው የማስተማር ሥነ-ዘዴ ሥልጠና ባለመውሰዳቸው እየተፈጠረ ያለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል ነው።

የመምህራን ሥልጠናው በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ የሚያበረክተው አስተዋጾ የጎላ  መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ  ለአንድ አካል የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

የትምህርት የልማት ግቦችን ለማሳካት ቢሮው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች በተፈጥሮና በማህበራዊ አፕላይድ ሳይንስ  ተመርቀው የማስተማር ስነ-ዘዴ ስልጠና የሚያስፈልጋቸው ከ2ሺህ በላይ መምህራን መኖራቸውን አስታውቀዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እጩ ዶክተር ካሳሁን ሙላቱ በበኩላቸው ስልጠና ከሚያስፈልጋቸው መምህራን መካከል 1ሺ 52 ለሚሆኑት የማስተማሪያ ዘዴ ስልጠና  እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው የትምህርት ተደራሽነትን በማረጋገጥ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ  በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ስልጠናውን ልምድ ባላቸው መምህራን በመስጠት የክልሉን የመምህራን አቅም ለማጎልበት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው በአጎራባች ዞኖች ከሚኙ የትምህርት ተቋማት ጋር የአቅም ግንባታ ተግባራትን ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ቀሪ ስልጠና የሚያስፈልጋቸውን መምህራን በቀጣይ ዙር ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታውቀዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የመማር ማስተማር ምክትል ፕሬዝዳንት እጩ ዶክተር ካሳሁን ሙላቱ  ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ደነቀ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የዩኒቨርስቲው የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም