በሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችሉ የታደሱ የሳንባ ካንሰር ምርመራ ክፍሎች በይፋ ተመረቁ

130

ግንቦት 10/2014/ኢዜአ/ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችሉ የታደሱ የሳንባ ካንሰር ምርመራ ክፍሎች በይፋ ተመረቁ።

በክፍሎቹ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ መመርመሪያ መሳሪያም ተተክሏል።       

አገር አቀፍ የሳንባ ካንሰር ምርመራና ቁጥጥር ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሥራ ገብቷል።

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የ'ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ' እና ጤና ሚኒስቴር ስምምነት ተፈራርመው ነው ተግባራዊ መሆን የጀመረው።       

ፕሮጀክቱ ዓላማው በካንሰር ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን የአቅም ግንባታ ስራዎች በተለይም በዘርፉ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ማጠናከር ይጠቀሳል።   

ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ ሌላው የፕሮጀክቱ ዓላማ ሲሆን በመስኩ የሚሰራውን ስራ የሚያጠናክር መሆኑም ነው የተገለጸው።        

የካንሰር ሶሳይቲው ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑንና 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተያዘለት የሶሳይቲው መስራች አቶ ወንዱ በቀለ ተናግረዋል።   

ፕሮጀክቱ እስካሁን በትግበራው ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው "ዛሬ በ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታድሰው ወደ ሥራ የገቡ 15 የምርመራ ክፍሎች ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል።   

አቶ ወንዱ እንደሚሉት፤ በፕሮጀክቱ የባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድግ ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን በአፋር፣ በኮምቦልቻ፣ በደሴ፣ በወሊሶ፣ በቱሉ ቦሎ እንዲሁም በአዲስ አበባ ባለሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፕሮጀክቱ የሳንባ ካንሰርን በተመለከተ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሆነም አክለዋል።

በካንሰር ሶሳይቲው አማካኝነት በኢትዮጵያ የካንሰር ሁኔታ አጋላጭ ምክንያቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሦስተኛ ዲግሪ የጤና ተማሪዎች ጥናት እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።    

የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል አርጋው በበኩላቸው በሆስፒታሉ የሚገኙ የምርመራ ክፍሎች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉ ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል።

በተለይ ዓለም ላይ የሳንባ ካንሰር ልየታና ህክምናው እየዘመነ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ራሄል በኢትዮጵያም ምርመራውን ለማጠናከር የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

"በሆስፒታሉ ለምርመራ የሚያገለግል ዘመናዊ መሳሪያ መተከሉም የምናደርገው የምርመራ ውጤት ትክክለኛነት የሚያሳድግ ነው" ብለዋል።  

እንደ ዶክተር ራሄል ገለጻ በህብረተሰቡ በኩል የዜጎች ቅድመ-ምርመራ ባህል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን አመልክተው ይህንን ባህል መቀየር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳንባ ካንሰር የስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ሌሊሳ አማኑኤል ናቸው።

በኢትዮጵያ ያለው የምርመራ ደረጃ በምን ላይ እንዳለ የተሻለ ለማወቅ ጥናት እንደሚጠይቅ ጠቁመው የምርመራ ክፍሎቹ ወደ ሥራ መግባት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ለዚህም "የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ" ከአጋሮች ጋር በመሆን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ ትግበራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም