የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሾመ

232
አዲስ አበባ ጶግሜ 3/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃን ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ። ፌዴሬሽኑ በዛሬው እለት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ፤ ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ የተጓደሉ አራት የስራ አስፈጻሚ አባላትን መርጧል። በዚህም ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ወይዘሮ ሰርካለም ከበደ፣ ዶክተር አይናለም አባይነህ፣ አቶ የኔነህ በቀለና አቶ ነጋሲ ኃለፎም በተጓደሉ የስራ አስፈጻሚ ቦታዎች ላይ መርጧል። ፕሬዚዳንት ሆነው  የተመረጡት ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃ ፌዴሬሽኑን በጊዜያዊ ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ በለጠ ዘውዴን በመተካት ያገለግላሉ። ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃ በከተማው የሚታየውን የእግር ኳስ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ በተለይም በክለቦች ምዝገባ ወጪና የህግ ክፍተት የሚታይባቸው ደንቦች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የገንዘብ አቅም የሌላቸው ክለቦችን የምዝገባ ወጪ በፌዴሬሽኑ በኩል እንዲሸፈን ለማድረግ ቃል ገብተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ኃይለሰማዕት ወርሃጥበብ፤ በበኩላቸው በከተማዋ ያሉት የማዘውተሪያ ቦታዎች ከወጣቶች ቁጥር ጋር የተመጣጠኑ እንዲሆኑ በ2011 ዓ.ም በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል። የአዲስ አበባን እግር ኳስ ስፖርት ማጠናከር ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገሪቷ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በፖሊሲዎችና በማዘውተሪያ ቦታዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራም አክለዋል። ጠቅላላ ጉባኤው በዛሬው እለት የ2010 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም፣ የኦዲት ሪፖርት፣ የፌዴሬሽኑ የማሻሻያ ደንብና የ2011 ዓ.ም እቅድ ላይ ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም