የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና የገንዘብ ሚኒስቴር ኤፍኤስዲ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያን ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

77

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና የገንዘብ ሚኒስቴር ኤፍኤስዲ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያን ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ፤የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ማሞ ምህረቱ እንዲሁም የኤፍ ኤስ ዲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ናፒየር ናቸው የተፈራረሙት።

የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያ ምስረታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ 30ኛው የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያ ይሆናል ተብሏል።

በገበያው ይፋዊ የሥራ መጀመሪያ ዝግጅት ላይ ባንኮችን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጨምሮ በትንሹ እስከ 50 ኩባንያዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንቸርፕራይዞች የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ተነድፏል።

በትብብር ስምምነቱ መሰረት ኤፍኤስዲ አፍሪካ ለቴክኒክ ድጋፍ፤ ለህግ ማማከር አገልግሎትና ሌሎች የሰነደ መዋዕለንዋዮች ገበያን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ይሸፍናል።