በክልሉ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከ900ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል

114

አዳማ ግንቦት 10/2014/ኢዚአ/ በኦሮሚያ ክልል በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከ900ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ዘጠኝ የበልግ አብቃይ ዞኖች 970ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ በሰብል ተሸፍኗል።

የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም ቀድሞ የእርሻ ማሳ ዝግጅት በመደረጉና 1 ነጥብ 2  ሚሊዮን ኩንታል የፋብሪካ ማዳበሪያን ጨምሮ የምርጥ ዘር አቅርቦት አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርስ በመደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

የበልግ እርሻው እቅድ ሙሉ በሙሉ መሳካቱን የገለፁት  ምክትል ሃላፊው በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ስንዴ፣ ገብስ፣ ቦቆሎን ጨምሮ የተለያዩ የአገዳ ሰብሎችና ጥራጥሬ መዘራቱን አመልክተዋል።

በዚህም ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንና  በአሁኑ ወቅት የዝናብ ስርጭቱ በደጋማ የክልሉ አካባቢዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል ።

"በዞኑ ከ150ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ አዝመራ ተሸፍኗል" ያሉት ደግሞ የአርሲ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ሁሴን ናቸው።

በዞኑ ከምርት ወቅቱ እርሻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ  መታቀዱን አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።

የፋብሪካ ማዳበሪያን ጨምሮ የስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎና ማሽላ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀድመው ተደራሽ በማድረጋቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የበልግ አዝመራ የዘር ስራውን ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል ።

"በዞኑ ከሚገኙ 26 ወረዳዎች ውስጥ በአብዛኛው የበልግ አዝመራ ልማት ይከናወናል"  ያሉትአቶ ሙስጠፋ "በአሁኑ ወቅት የእርሻ ማሳዎችን በሰብል ዘር የመሸፈን ስራ ተጠናቆ ቡቃያውን የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ጀጁ ወረዳ ሄጦ ፈርዳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ አደም "ዘንድሮው የበልግ ዝናብ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም ወቅቱን ተጠቅመን ማሳችንን በዘር የመሸፈን ስራ አጠናቀናል" ብለዋል ።

የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ቢኖርም የምርጥ ዘር አቅርቦት መኖሩን ያመለከቱት ደግሞ የቀርሳ ሞለሜ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል አሊይ ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ቀድመው የዝግጅት ስራ በማጠናቀቃቸው ዝናብ ሲዘንብ ቀጥታ ወደ ዘር መዝራት ገብተው ስራውን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም