በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው-የጤና ሚኒስቴር

251

ግንቦት 9/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ከፍተኛ የደም ግፊትን ጨምሮ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም የከፍተኛ የደም ግፊት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ “ደም ግፊትዎን በትክክል ይለኩ፤ ደም ግፊትዎን ይቆጣጠሩ እና ረጅም እድሜ ይኑሩ!” በሚል መሪ ሀሳብ  በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

ቀኑን የተመለከተ መርሃ ግብር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ማይጨው ጤና ጣቢያ ዛሬ ተካሄዷል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 31 በመቶ የሚሆኑት በልብ ነክ በሽታዎች መሆኑንና በኢትዮጵያም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ገዳይነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 43 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አማካኝነት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ አድርገው አመልክተዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ጨው የበዛባቸውን ምግቦች በመቀነስ፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግና የደም ግፊት ምርመራን ባህል በማድረግ ከበሽታው ራሱን መከላከል እንዳለበት ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በ300 ጤና ጣቢያዎች ላይ የሚያስፈልጋቸውን ግብአት በማሟላት ደረጃቸውን የጠበቁ የደም ግፊት ምርመራ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግን ጨምሮ መንግስት ከፍተኛ ደም ግፊት በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳጁማ ያደታ በበኩላቸው ለልብ በሽታ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ዋነኛው ደም ግፊት በመሆኑና ግፊቱን ሊጨምሩ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል

የዓለም የከፍተኛ የደም ግፊት ቀንን በማስመልከት ዛሬ በአዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች፣ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮች እና በክልሎች ነጻ የደም ግፊት ምርመራ ሲደረግ መዋሉ ተገልጿል።

ከፍተኛ የደም ግፊትደም ከልብ በከፍተኛ ግፊት በደም ቧንቧዎች አማካኝነት ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል ሲረጭና ይህም ከተለመደው የደም መርጨት ተግባር በላይ ሲሆን ይከሰታል።

በዓለም እድሜያቸው ከ30 እስከ 79 እድሜ ክልል የሚገኙ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሰዎች በላይ ሰዎች የደም ግፊት እንዳለባቸውና ከነዚህም ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚገኙት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በዓለም ላይ ከደም ግፊት ጋር የሚኖሩ 42 በመቶ ገደማ ሕመምተኞች ግፊታቸው ሊድንና ሊታከም የሚችል መሆኑን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም