ድርቅን ለመቋቋም በተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች የተገነቡ 87 የውሃ ፕሮጀክቶች በቀጣዩ ወር ስራ ይጀምራሉ

96

ግንቦት 8/2014 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ድርቅን ለመቋቋም በተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች የተገነቡ 87 የውሃ ፕሮጀክቶች በቀጣዩ ወር አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተገለጸ።

ፑንትላንድ ግዛት የመጣ የልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች እየተገበረ ባለው የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ስር የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።    

ፕሮጀክቱ በ451 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚተገበር ሲሆን ከዚህም ውስጥ 350 ሚሊዮን ዶላሩ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ እንደሚሸፈን ተጠቅሷል፡፡

90 ሚሊዮን ዶላሩ ከግብርና ልማት ፈንድ/ኢፋድ/ እንዲሁም ቀሪው ወጪ ከህብረተሰቡ በሚገኝ ገቢ የሚሸፈን ይሆናል፡፡

ፕሮጀክቱ  ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን በአጠቃላይ በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህም በስድስት ክልሎች የሚገኙ 100 ወረዳዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሰኢድ ዑመር እንደተናገሩት፤በፕሮጀክቱ ስትራቴጂክ ተብለው የተለዩ የውሃ፣የመስኖ፣የመንገድ ጨምሮ 53 ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ።  

እስከ ሚቀጥለው ዓመት ድረስ 210 ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እቅድ መውጣቱንም ነው ያስረዱት፡፡  

በ1500 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ልማት እየተከናወነ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ከድርቅ ጋር በተያያዘም በ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች 87 የውሃ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣዩ ወር ለአገልግሎት እንደሚበቁ ተናግረዋል።  

አቶ ሰኢድ እንደሚሉት፤ ወጣቶችና ሴቶችን በቁጠባና ብድር ማደራጀት ስራ መከናወኑን ጠቁመው ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራም እየተሰራበት መሆኑን አብራርተዋል።  

ፕሮጀክቱ ከተካተቱ መርሃ-ግብሮች መካከል የማህበረሰብ ልማት አንዱ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አነስተኛ መስኖዎችን ጨምሮ የጤና ኬላና ትምህርት ቤት ግንባታዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በመርሃ-ግብሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ፑንትላንድ ግዛት የመጣው ልዑክ አባላት በሰጡት አስተያየት በቆይታቸው በርካታ ተሞክሮዎችን መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ካፊሚደምዲም አደም ኢትጵያና ፑንትላንድ ተመሳሳይ የአየር ጠባይ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የልዑክ ቡድኑ ችግሮችን በጋራ ለማለፍ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በነበረን ጉብኝት ብዙ ነገሮችን ተምረናል በቀጣይ የገኘናቸውን መልካም ተሞክሮዎች ተግባራዊ ለማድረግ እንሰራለን ሲሉም አክለዋል።   

እኛም በፑንትላንድ ቆላማ አካባቢዎች ፕሮጀክት ዙሪያ ያለንን ልምድ ለኢትዮጵያ አካፍለናል ብለዋል።

ሌላኛዋ የልዑኩ አባል ማሪያም መሀመድ አደም በበኩላቸው በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የኑሮ ማሻሻያ ስራዎች ትልቅ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን አይተናል ሲሉ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም