አዲሱ ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው---የዘርፉ ምሁራን

218
ባህር ዳር ጶግሜ  3/2010 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ምሁራን ገለፁ። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ  ያዘጋጀውና በአዲሱ አገር አቀፍ የትምህርትና ሰልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ከዘርፉ አመራሮች ጋር ለሁለት ቀን ያዘጋጀው የውይይት መድረክ  በባህርዳር  ከተማ ተካሄዷል። ፍኖተ ካርታውን ካዘጋጁት መካከል በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የመምህራን ስልጠና ባለሙያና መምህር ዶክተር ዳዊት አስረስ በተዘጋጀው ካርታ ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ፅሁፍ ለባለድርሻ አካላት አቅርበዋል ። በዚሁ ጽሁፋቸው እንደተመለከተው  አሁን በስራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ  የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባና ከትምህርት ጥራት ይልቅ ሽፋን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ። የትምህርት አሰጣጡም የውጪ ሀገራት ፖሊሲ ላይ ትኩረት ያደረገና ከተግባር ይልቅ ንድፈ ሃሳብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ስራ ፈጣሪ ትውልድ ከማምጣት አኳያ ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል ። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ያለውጤት ከክፍል ክፍል እንዲያልፉ የሚፈቅድና መሰል ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ የትምህርትን ጥራት በማስጠበቅ ብቁና የሀገሩን ችግር በራሱ የሚፈታ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ ክፍተት እንዳለበት በጥናት መረጋገጡን አስታውቀዋል። በጥናቱ  መሰረት ፖሊሲው እንዲቀየር በመታመኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር መቅረቡን ገልፀዋል ። " ፎኖተ-ካርታው ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታተሙ የመማሪያ መጻህፍትና የሚቀረፁ ስርአተ ትምህርቶች የሀገሪቱን ባህልና ወግ ያገናዘቡና በተግባር የተደገፉ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው"ብለዋል ። የትምህርት ጥራትን ለመቀየር መጀመሪያ ደረጃ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ ያስረዱት ዶክተር ዳዊት አዲሱ የትምህርት ፎኖተ-ካርታ  ማንኛውም  የደረጃው ተማሪ  ማንበብ፣ ማስላትና አካባቢውን እንዲያውቅ  የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። ካርታው ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች የሚሰጡበትና በማህበራዊ የትምህርት ዘርፎችም ትውልዱ የሀገሩን ባህል እንዲያውቅ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን  ዶክተር ዳዊት በፅሁፋቸው አመላክተዋል። በበቂ ቤተ- ሙከራና የሰው ኃይል ያልተደራጁ የከፍተኛ ትምህርትና  የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዳይከፈቱ ፍኖተ ካርታው ይከላከላል። " በፍኖ ካርታው  ብሄራዊ ፈተናዎች በስምንተኛና 12ኛ ክፍል ይሰጣሉ “ ያሉት ዶክተር ዳዊት ፍኖተ ካርታውን ተግባር ላይ ለማዋል በሁሉም ክልሎች እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ ባለሙያዎች ምክክር እየተደረገበት መሆኑንም አስታውቀዋል ። የአማራ ክልል ትምህት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው እሁን ያለው የትምህርት ስርዓት ክልሉንም እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል ። " የትምህርት አሰጣጡ  በንድፈ ሃሳብ ላይ ያተኮረ በመሆኑ እንደ ክልል የተማረው የሰው ኃይል ስራ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ ጠባቂና ተቀጣሪ እንዲሆን አድርጎታል"ብለዋል ። በክልሉ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና  ፎኖተ-ካርታ ተግባር ላይ ለማዋል እስከ ወረዳ ድረስ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተደረገበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። ፎኖተ-ካርታው  የሀገሪቱን  ነባራዊ  ሁኔታ ከግምት ያስገቡ ጭብጦችን የያዘ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሰራ ዶክተር ይልቃል አመልክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም