ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል --ምሁራን

81

አርባ ምንጭ ግንቦት 9/2014 (ኢዜአ) ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ምሁራን አስገነዘቡ።

ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሰሞኑን  በአርባ ምንጭ  ዩኒቨርሲቲ  በተካሄደው  8ኛው አገር አቀፍ  አውደ ጥናት  ላይ የተሰተፉ አንዳንድ ምሁራን  ለኢዜአ  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ካሱ ጡሚሶ እንዳሉት የአገሪቱን አንገብጋቢ ችግሮች  በምክክር ለመፍታት የችግሮቹን ምንጭ መረዳት አስፈላጊ ነው።

"የፖለቲካ፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ብዝሃነቶች ቢኖሩንም የምንኖረው በአንድ አገር በመሆኑ  በሀገር ጉዳይ ልንደራደር አይገባም" ብለዋል።

ባለፉት አመታት ከዜጎች አንድነትና አብሮነት ይልቅ በልዩነት ላይ ትኩረት  ተሰጥቶ ሲሰራ በመቆየቱ  አሁን ለሚስተዋሉ ችግሮች  መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

"በምክክሩ ወቅት አብሮነትንና ሀገራዊ አስተሳሰብ እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች በሚፈቱባቸው አግባብ  ላይ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ምሁራን በጋራ አንድ አቋም በመያዝ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ  ዘርፎች  ስኬታማ የማድረግ ምሁራዊ  ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ጠቁዋል።

አገራዊ ምክክሩ እንደ አገር ከገባንበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የምንወጣበት ትልቅ መሣሪያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና  ቅርስ አስተዳደር  ትምህርት ክፍል  መምህርት ሃይማኖት ዓለማየሁ ተናግረዋል።

"ምክክሩ  ለግጭት መንስዔ የሆኑ ችግሮች ተለይተው በሚፈቱባቸው ላይ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቅንነት መሳተፍ   በሚችልባቸው  ሁኔታዎች ላይ  መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊና የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ንጉስ ሽመልስ በምክክሩ  ላይ የሁሉም  ሃሳብ እንዲካተት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

"በተለይ ፅንፈኝነት የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶችን የሚሸረሽርና የሚነጣጥል በመሆኑ በአገራዊ ምክክሩ ከምንም በላይ ብሄራዊ ጥቅማችንን ልናስቀድም ይገባል " ብለዋል።

የተቋቋመው ኮሚሽን በሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማዳመጥና ህዝቡ የሚለውን ሃሳብ ማስተናገድ  እንዳለበት ተናግረዋል።

በመድረኩ የችግሮችን መሠረት በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም