የደቡብ ወሎ ዞን ተፋሰሶች ልማት ለስራ አድል ፈጠራ እያበረከቱ ነው

155

ደሴ  ግንቦት 9/2014 /ኢዜአ/ በደቡብ ወሎ ዞን ተፋሰሶችን በማልማትና በመጠበቅ የስራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዞኑ ደሴ ዙሪያ ወረዳ በበጋ ወራት የለማውን የጠባሴ ሞዴል ተፋሰስ እየጎበኘ ነው።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዞኑ 1ሺህ 300 በላይ ተፋሰሶች ከ43 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል።

በልማቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰው መሳተፉን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ ጠቀሜታውን ተገንዝቦ በራሱ ተነሳሽነት ጭምር በማሳው ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ በ46 ሞዴል ተፋሰሶች ለ2 ሺህ 760 ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁን ለ285 ወጣቶች ተላልፏል።

በሞዴል ተፋሰሶች ላይ ወጣቶች የሚተክሉት ከ680 ሺህ የደጋና የቆላ ፍራፍሬ ችግኝ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው ተፋሰሶችን በማልማትና በመጠበቅ የስራ እድል መፍጠራያ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለተፋሰሶች ልማት ህገ ደንብ ወጥቶላቸው ለወጣቶች እየተላለፉ መሆኑን ጠቁመው፤ የውሃ አማራጭ ኖሯቸው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲለማባቸው እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአቶ ዑመር ሁሴን የተመራው የሥራ  ኃላፊዎች ቡድን በለጋምቦ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማውን ስንዴ ጎብኝቶ በወረ ኢሉ ወረዳ ለሚገነባው የግብርና ምርምር ግንባታ ማዕከል መሰረተ ድንጋይ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

በጉብኝቱ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢኮናሚ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም