የሀገርን አንድነትና ሠላም ለማሰጠበቅ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ተሳትፎ የላቀ ሚና አለው

487

ሚዛን አማን፤ ግንቦት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገርን አንድነትና ሠላም ለማሰጠበቅ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት የወጣቶች ተሳትፎ የላቀ ሚና እንዳለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቦንጋ ከተማ ከሚገኙ ወጣቶችና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

"የዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሁለንተናዊ ብልፅግና"  በሚል መሪ  ቃል የተካሄደው ውይይት በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር ያለመ ነው።

ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የሀገርን አንድነትና ሠላም ለማሰጠበቅ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት የወጣቱ ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው።

ወጣቱ ትውልድ የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የዛሬዋን ሀገር የመምራትና የማቃናት ዕድሉ በእጁ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ለዘላቂ ሠላምና ልማት የራሱን አሻራ ሊያስቀምጥ ይገባል ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድ ምክንያታዊ አስተሳሰብን በማጎልበት የአካባቢውንና የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ዘላቂነት እንዲኖረው የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቶች  ያላቸውን እምቅ አቅም በሀገር ግንባታ ላይ  እንዲያውልም ጠይቀዋል።

መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የመገናኛ ብዙሃን ሚና የላቀ መሆኑን መስተዳደሩ ገልጸው፤ ለሀገር ግንባታ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ  ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ለሀገርና ለህዝብ የማይጠቅሙ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየለቀቁ ህብረተሰቡ በልማትና ሰላም ላይ እንዳያተኩር የሚያደርጉ አካላትን ወጣቶች በፅናት መታገል አለባቸው ብለዋል።

የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የህብረተሰቡ ለስቃይና እንግልት እያደረጉ ያሉ የክልሉ አመራሮች ላይ የክትትልና የቁጥጥር  ስራዎችን በማጠናከር እርምጃ እንደሚወሰድም አረጋግጠዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው "ወጣቱ  ማበርከት ያለበትን ድርሻ መወጣት ከቻለ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካሞ አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነውም ብለዋል።

በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን ያነሱ የውይይቱ ተሳታፊዎች የኑሮ ውድነትና የማህበራዊ ሚዲያዎች ሥርዓት እንዲይዙ እንዲደረግም አሳስበዋል።

ለወጣቶች ተሳትፎና ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በማይሰጡ አመራሮች ላይም ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

በየደረጃው መፈታት ያለባቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጊዜ ሳይሰጣቸው መፍትሄ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል ሲል ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም