ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች

86

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትብብር በማጠናከር ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የሚኖራትን ሚና አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ሶማሊያ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ናቸው።

የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ትብብር እንዲሁም የልማት ትስስራቸው ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በጎረቤት አገር ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የኢትዮጵያ ድጋፍና እገዛ እስካሁንም የዘለቀ መሆኑን ጠቅሰው ሶማሊያ ሰላማዊ ምርጫ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያካሄደችውን የስልጣን ሽግግር ኢትዮጵያ ታደንቃለች ብለዋል።

የሶማሊያ ሰላማዊ የምርጫ ሂደትና የስልጣን ሽግግር ለሶማሊያውያን ኩራት ሲሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በአዲሱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ከሚመራው መንግስት ጋር በቅርበት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማጠናከር በተጨማሪ ድህነትን በመዋጋትና ድርቅን በመከላከል እንዲሁም በቀጣናው የልማት ትስስርን በማጎልበትና የጋራ ጠላት የሆነውን ሽብርተኝነት በጋራ እንዋጋለን ብለዋል።

በኢኮኖሚ ውህደት በንግድ፣ በመሰረተልማት ትስስስርና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

አዲሱ የሶማሊያ መንግስትም ኢትዮጵያ ያላትን የትብብር ፍላጎትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተፈጻሚ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እናምናለን ነው ያሉት።

"ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ከፍተኛ የህይወት ዋጋ ከፍላለች" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በቀጣይም ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ከአዲሱ መንግስት ጎን ትቆማለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተለይም አሸባሪውን አልሸባብ ለማስወገድ ለሚደረገው ማንኛውም እርምጃ የኢትዮጵያ ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለኢጋድ ብሎም ለአፍሪካ ህብረት የጋራ የልማት እቅድ ስኬት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የምትሰራ መሆኑንም አምባሰደር ዲና ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲጠናከርና ለስኬት እንዲበቃ ትብብራችንን እንጠናክራለን ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በየብስና በአየር ትራንስፖርት እንዲሁም በኃይል ዘርፍ የተጀመሩ ትስስሮች የላቀ ውጤት ላይ እንዲደርሱም ይሰራል ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት የተራዘመው የሶማሊያ ምርጫ ትናንት በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ተካሂዷል።

በዚህም ሶማሊያን ከፈረንጆቹ 2012 እስከ 2017 የመሯት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በስልጣን ላይ ያሉትን ሞሃመድ አብዱላሂ መሀመድ (ፋርማጆ) በማሸነፍ 10ኛው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት  ሆነዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ወንድም የሶማሊያ ህዝብ በድምጻቸው የሚፈልጉትን መንግስት በመምረጣቸው የእንኳን ደስ ያላቸሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም