በአፋር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ነው

138

ግንቦት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በአገር አቀፍ ደረጃ በትግበራ ላይ የሚገኘው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ድርቅን በመቋቋም ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደሮች ገለጹ።

ከፑንትላንድ ግዛት የመጡ ልዑካን ቡድን አባላት በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተከናወኑ ተግባራትን ጎብኝተዋል።        

ልዑኩ በኦሮሚያ፣ አፋርና ሱማሌ ክልል የተከናወኑ ተግባራትን ተሞክሮ ቀስሟል።     

ልዑኩ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የእንስሳት መኖ ልማት እንዲሁም በጸሃይ ኃይል የሚሰራ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራዎችን ተመልክተዋል።  

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርብቶ አደሮችም በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሆነው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ድርቅን በመቋቋም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል፤ አብዱል ሄሩ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የበዳዓሌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።     

ከዚህ በፊት በአካባቢው ድርቅ እየተከሰተ ከብቶች እየሞቱ ነበር፤ አሁን ግን በፕሮጀክቱ አማካኝነት መኖ እየቀረበ በመሆኑ ከችግር እየወጣን ነው ያሉት።      

በሃያ ሄክታር ላይ እየለማ ካለው ቶሎ የሚደርስ የሳር ዘር እስካሁን ለሦስት ዙር ያህል ምርት ተጠቅመናል ብለዋል።   

"ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ከባድ ነበር ይሄ የእንስሳት መኖ ባይደርስልን ኖሮ ከብት የሚባል ነገር አይኖርንም ነበር" ነው ያሉት።      

ሌላው ተጠቃሚ አቶ አብዱ ናስር በበኩላቸው የመኖ ልማቱ ድርቅን ከመቋቋም ባለፈ የሥራ እድል እንደፈጠረላቸው አብራርተዋል።  

የአፋር ክልል ቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ደረሰ ዓሊ እንደተናገሩት፤ የአርብቶ አደርሩን ኑሮ ለማሻሻል በመሰረተ ልማት፣ በውሃ አቅርቦትና የእንስሳት መኖ አቅርቦት ላይ በስፋት እየተሰራ ነው።  

በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

ከእንስሳት መኖ ልማት ጋር በተያያዘ በተያዘው ዓመት እስከ 400 መቶ ሄክታር መሬት ላይ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሳር ለማልማት ግብ መጣሉንም አብራርተዋል።

እስካሁን 300 ሄክታር ላይ ማልማት መቻሉን የተናገሩት አስተባባሪው ምርቱን በየወረዳው እየተከፋፈለ መሆኑን አስረድተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሆነው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ለስድስት ዓመት ገቢራዊ የሚሆን ሲሆን እስካሁን ሁለት ዓመት ከግማሽ የሚሆን ጊዜ አሳልፏል።

ፕሮጀክቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በስድስት ክልሎች በ450 ሚሊዮን ብር የሚተገበር ሲሆን ከዚህም 350 ሚሊዮኑ ከዓለም ባንክ፣ 90 ሚሊዮኑ ከዓለም አቀፍ ግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ)ና 11 ሚሊዮኑ ደግሞ ማኅበረሰቡ በገንዘብና በአይነት የሚደግፈው ነው ተብሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም