በአዲሱ ዓመት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ዋነኛ ትኩረት ነው ---የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

55
መቀሌ ጶግሜ 3/2010 መጪውን አዲስ ዓመት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር የመንግስት ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡ ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  ይህንን የገለጹት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት የአዲሱን ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ሰማዕታት ሀወልት አደራሽ ዛሬ በተዘጋጀው ስነሰርዓት በተገኙበት ወቅት ነው፡፡ ፡ ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ አልፎ በተለያዩ ሀገራት እያሳየ ያለውን በጎ ተግባር ካለው ህዝባዊ ወገንተኛነት የሚመነጭ  እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም አኩሪ ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰው "ሀገራችን የጀመረችውን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል "ብለዋል፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር የመንግስት ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም መንግስት የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። " በሀገራችን ተከስተው በነበሩት ሁከትና ግጭቶች ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ስራዎች በመጪው ዓመት እንዲያንሳራሩ ይደረጋል" ብለዋል፡፡ ፈጣን ልማትን  ለማስቀጠልም መንግስት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መጪው ዓመት ለሀገሪቱ ህዝቦች የሰላም፣ የጤናና የብልፅግና እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸው ገልጸዋል። " የመከላከያ ሰራዊታችን  የህገመንግስቱን መርሆዎች እንደ ምሰሶ በመያዝ ህዝባዊነቱን ዳግም አስመስክሯል "  ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል  ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ባሉት ሁከትና ግጭቶች ለመቆጣጠር መከላከያ ሰራዊቱ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የበዓል ስነስርዓት  ከመከላከያ ሰራዊት በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች የተሰናበቱ እንዲሁም ሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችና የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም