የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያሰባሰበውን ከ5ሺህ በላይ መጻህፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረከበ

173

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከተቋሙ ሠራተኞችና ከሌሎች አካላት ያሰባሰበውን ከ5ሺህ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት አስረከበ።

ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት "ሚሊዮን መጻህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ መጻሕፍትን የማሰባሰብ ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ምላሽ እየሰጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በዛሬው ዕለት ከተቋሙ ሠራተኞችና ከሌሎች አካላት ያሰባሰበውን ከ5ሺህ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረክቧል።

መጻሕፍቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ ለአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር የመንግሥ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ አስረክበዋል።

ኢዜአ በመጀመሪያ ዙር ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ያሰባሰባቸው መጻሕፍት በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

ከዚህም ጎን ለጎን በኪነ-ጥበብ፣ በህክምና፣ በጋዜጠኝነትና ተግባቦት ላይ ያተኮሩ በርካታ መጻህፍት መኖራቸውን በመርኃ ግብሩ ተጠቁሟል።

ኢዜአ በቀጣይ ሁለተኛው ዙር የመጻሕፍት ማሰባሰብ መርኃ ግብር እንደሚያካሂድ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሠይፈ ደርቤ አረጋግጠዋል።

በርክክብ መርኃ ግብር ላይ ገጣሚና ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱና ደራሲ ተስፋዬ ርስቴ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም