የህንጻ ግንባታዎችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ተፈፃሚ እየሆነ አይደለም

229
አዲስ አበባ ጰጉሜ 3/2010 በአገሪቱ የሚገነቡትን ህንፃዎች የግንባታ ሂደትና ጥራት ለመከታተልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 624/2001 በትክክል ስራ ላይ መዋል አልቻለም። የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህንጻ አዋጅ ቁጥር 624/2001 ከ 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ቢያደርግም አፈፃፀሙ ግን ጉራማይሌ ሆኖ ይስተዋላል። በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ህግጋት ዝግጅትና አፈጻጸም ክትትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለዜጎች ጤናና ደህንነት ተብሎ የወጣው የህንፃ አዋጅ በትክክል እየተተገበረ አይደለም። አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም በመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ ተፈፃሚ መሆን አለመቻሉን ጠቁመዋል። ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ጀምሮ አብዛኞቹ የመንግስት ፕሮጀክቶች በሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ ሳያገኙና ሳይጸድቁ በባለስልጣናት ፖለቲካዊ ውሳኔ ቀጥታ ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። "የመንግስት ባለስልጣናት ወደ አንድ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፤ ከዚህ ቦታ ትምህርት ቤት ወይም ሌላ ፕሮጀክት ይጀመር የሚል ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ አዋጁን ያልተከተለ ግንባታ ይገነባሉ" ነው ያሉት። የህንፃ ግንባታ ስምምነት ሳይዙ ከህንፃ ሹም ፈቃድ ስለማይሰጣቸው ከህንፃ አዋጁ ውጭ በሆነ መንገድ የሚገነቡ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ የግንባታ ሂደቱን ለመቆጣጠርና ለመከታተል መቸገራቸውን ተናግረዋል። አንዳንድ የመንግስት ተቋማት የህንፃ ቁጥጥሩን፣ የግንባታ ኮንትራት አስተዳደር ስራውን እንዲሁም የክፍያውን ሂደት በሙሉ በመቆጣጠራቸው  ግልጽ የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን ፈታኝ እንደሆነ አመልክተዋል። በመሆኑም የዲዛይን፣ የኮንትራት አስተዳደርና ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን የዕለት ተዕለት ስራ ለአማካሪዎችና ተቋራጮች በመስጠት የቁጥጥር ስራውን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በመንግስት ያልተከበረውን አዋጅ ህዝቡ እንዲያከብረው ማድረግ ከባድ ፈተና በመሆኑ አዋጁን ተፈፃሚ ለማድረግ በቅድሚያ በመንግስት በኩል የእርምት ርምጃ መወሰድ እንዳለበት ገልጸዋል። በቀጣይ የሚወጡት ህጎች መመሪያዎች በወጡበት ደረጃ በትክክል እየተተገበሩ መሆናቸውን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ኦዲት ለማድረግ እቅድ መያዙን የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም