አገራዊ ምክክሩ ግልጽና ተደራሽ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው

159

ግንቦት 6/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን የምክክር ሂደቱ ግልጽና ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር አገራዊ ምክክሩ አገሪቱን ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ ምዕራፍ እንደሚያሻግራት ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ መገናኛ ብዙኃን ከኮሚሽኑ መቋቋም ጀምሮ የአገራዊ ምክክር አስፈላጊነትን በተመለከተ ሕዝቡን የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ርብርብ ሊያደረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን የምክክር ሂደቱን ግልጽና ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ምክትል ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ እንደገለጸው፤ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ሂደቱን የተመለከቱ መረጃዎች ተደራሽ መሆን አለባቸው።

አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ ግልጽና ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የመገናኛ ብዙኃን ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት አሻራቸውን ማኖር እንደሚገባቸው ምክረ-ሃሳብ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ፤ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታም መገናኛ ብዙኃን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብሏል።  

የሚዲያ ተቋማት አገራዊ ምክክሩ በግብ ደረጃ የያዛቸው ጉዳዮች ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባና ለምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ተናግሯል።

ሂደቱን ሊያሳካ የሚችል ልዩ ዕቅድ በማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በመጠቆም።

እርሳቸው የሚመሩት ተቋምም ይህንን ታሪካዊ ሂደት በመደገፍ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የናሁ ቴሌቪዥን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በበኩላቸው፤ በአገራዊ ምክክሩ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍና የተፈለገው ውጤት እንዲገኝ መገናኛ ብዙኃን መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ተቋማቸውም (ናሁ) ለዚህ አገራዊ ምክክር ስኬት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አረጋግጠዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሰሞኑን አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የመገናኛ ብዙኃን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም