የደቡብ ክልል በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ከምዝበራ አዳነ

100

ሀዋሳ፣ ግንቦት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በሙስና ሊመዘበር የነበረ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ሀብት ማዳን መቻሉን የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ምክትል ኮሚሽነር  አቶ አማኑኤል አብደላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀብቱን ከምዝበራ ማዳን የተቻለው ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተካሄደው አስቸኳይ ሙስና የመከላከል ስራ ነው።

አብዛኛዎቹ ሀብት ሊመዘበር በሂደት ላይ እያለ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት የዳኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ ሙስናን በመካከል ላይ ያተኮረ ጥናቶች በማካሄድና ወደ ትግበራ በመቀየር የተገኙ ውጤቶች እንደሆኑ ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያመለከቱት።

በዚሁ እንቅስቃሴ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከጨረታ፣ ከመንግሥት እቃ ግዥዎች እና ከመሬት ጋር የተያያዙ ምዝበራዎችን ማስቆም መቻሉን አስረድተዋል።

በተለይ በየደረጃው በተደረገው ማጣራት በደላላ፣ በአመራርና በመሐንዲሶች የተመዘበረ 26 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉን ለአብንት ጠቅሰዋል።

የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ የማይጋበዝ ተጫራች ጨረታ አሟልተዋል ተብሎ እና ቃለ ጉባኤ ተይዞ ቅድመ ክፍያ የተፈጸመን 8 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ሀብት እንዲመለስና ጨረታው እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል።

ሙሰኞችን ለህግ በማቅረብ ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር የመክሰስና የመመርመር ስልጣን ካላቸው የፍትህ አካላት ጋር ኮሚሽኑ በአጋርነትና በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ አማኑኤል አስታውቀዋል።

ሙስናን በመከላከሉ ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የሚሰጡ ጥቆማዎችም በአብዛኛዎቹ ጥራቱን የጠበቀ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ የያዙ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ በገጠር ቀበሌያት የሚፈጸም የመሬት ወረራ በጥብቅ እየተከታተለ ለአቅራቢያውና ለክልሉ ለሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ በመስጠት የላቀ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ ሌብነትን እንዲታገል ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት የክልሉ ህብረተሰብ ሙስናን እየታገለ እንደሆነ ገልጸው፤ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት  በመንግስት ግዢ፣ በንግድና ትራንስፖርት፣ መሬት አስተዳደር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አተኩሮ ሙስናል ለመከላከል እየሰራ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ በየደረጃው በሚገኙ ፍትሕ ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ብለሹ አሠራሮችን ለመከላከልም አቅዶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚዘጋጁ ቦታዎችና የሚመደብ ሀብት ከዓላማው ውጪ እንዳይባክን ለማድረግም አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑም እንዲሁ።

በደቡብ ክልል በ2013 በጀት ዓመት ሙስናን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉን ከምክትል ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም