በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀልና ግድያን በማስቆም በመላ አገሪቱ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው

116

ግንቦት 6/2014 (ኢዜአ) ጽንፈኝነትና ፖለቲካዊ መገፋፋት በሚፈጥራቸው ድርጊቶች በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀልና ግድያን በማስቆም ሰላም ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ መንግሥት የዜጎችን ሠላም ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ጽንፈኝነትና ፖለቲካዊ መገፋፋት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀልና ግድያን በማስቆም በመላ አገሪቱ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

መንግሥት እየወሰደ ባለው ሕጋዊ እርምጃም አዎንታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጎንደር ከተማ በመቃብር ሥፍራ ተከስቶ የነበረው ግጭት ኅዝቡን ባሳተፈ መልኩ ከድርጊቱ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስ መቆጣጠር መቻሉን አንስተዋል።

የኃይማኖት አባቶችንና ወጣቶችን በማሳተፍም የተዘረፉ ንብረቶችን ማስመለስ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ-እምነቶች መልሶ ለመገንባት የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

በድርጊቱ የተሳተፋ አካላትንም ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በክልልና በጸጥታ ኃይሎች ጥምረት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ጎን ለጎንም፤ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልልም አሸባሪዎቹን የአልሸባብና ሸኔ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ ጋርም በቤተ-እምነቶች ጭምር የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አንስተዋል።

በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዳይሰፍን፣ የአማራ ህዝብ ሰላም ውሎ እንዳያድር ሆን ብለው በሚሰሩ አካላት ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመላክተዋል።

የክልሉ መንግሥትም ለአገራቸው ሉዓላዊነት መከበር መስዋዕት ለከፈሉ አካላት እውቅና መስጠቱን የሚመሰገን እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የሸኔ አሸባሪ ኃይል ላይም ህዝቡን ያሳተፈና በልዩ ኮማንዶ የታገዘ ውጤታማ ኦፕሬሽን እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እየተወሰደ በሚገኘው ኦፕሬሽንም የሽብርተኛው ሸኔ አመራርና አባላት እየተደመሰሱ መሆኑን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል መንግሥት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ በየብስና በአየር የታገዘ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተያዘው ሳምንትም 165 ተሽካርካሪዎች መቀሌ መድረሳቸውንም በመጠቆም።

የሕወሃት የሽብር ቡድን ወራሪ ኃይል የአፋር የተለያዩ አካባቢዎችን በመያዝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በያዛቸው የአፋርና አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ለሞትና ስቃይ እየዳረገ በሚገኝበት ወቅት የሚነዛው የተከብቤያለሁ ፕሮፖጋንዳ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማቃለልም እንደ ስንዴ፣ ዘይትና ሌሎች መሰል የፍጆታ እቃዎች በፍራንኮ ቫሎታ በኩል የሚገቡበት መንገድ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

የዋጋ ግሽበቱን በዘላቂነት ለመፍታትም ከ700 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ስንዴ እንዲሸፈን በማድረግ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ሲሆን ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም