ማህበሩ ለተፈናቃይ ወገኖች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

80
መቀሌ/ሽሬ እንዳስላሴ ጳጉሜ 3/2010 የትግራይ  የጦር አካል  ጉዳተኞች ማህበር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ለተፈናቀሉ ወገኖች  የአንድ ሚሊዮን  ብር ድጋፍ አደረገ። በሌላ በኩልም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ   አዲሱ ዓመት ምክንያት በማድረግ  ለችግረኛ ወገኖች የአልባሳት ፣ የገንዘብና የዳቦ ዱቄት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የማህበሩ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አፅበሃ አረጋዊ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲውል ገንዘቡን ትናንት ለክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አስረክበዋል፡፡ በርክክቡ ወቅት  አቶ አጽበሃ እንዳሉት ያደረጉት  የገንዘብ ድጋፍ  ማህበሩ ባለው አቅም የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ የድርሻቸውን ለመወጣት ነው፡፡ " የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂ ለማቋቋም ሁሉም የህብረተስብ ክፍል ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የተፈናቀሉ ዜጎች ለማገዝ ማህበሩ  ያደረገው ድጋፍ ለሌችም አርአያ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ  ኪሮስ ሀጎስ ናቸው፡፡ የተሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ለተፈናቃይ ወገኖች እንደሚውል የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊዋ እንዳመለከቱት ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም  ግማሽ ቢሊዮን ብር ከህብረተሰቡ ለማሰባሰብ  ታቅዶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ለሚገኙ ከአራት መቶ በላይ ችግረኛ ወገኖች አዲሱ ዓመት ምክንያት በማድርግ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የከተማዋ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አሚና ሙሳ እንዳሉት የተደረገው ድጋፍ  አልባሳት፣ገንዘብና የዳቦ ዱቄት ሲሆን ድጋፉ ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች  በስጦታ የተገኘ ነው። በዚህም ለ265 ሰዎች የአልባሳት፣ ለ100  የገንዘብ እና ለ44 ሰዎች  ደግሞ የዳቦ ዱቄት ድጋፍ ተደርጓል። አልባሳቱ በስጦታ ያበረከተው የጉና የንግድ ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን የዳቦ ዱቄቱን የለገሱት ደግሞ  አቶ ተክኤ አበራ  የተባሉ ባለሀብት ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም