ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዳይሆን ካደረገው የአካታችነት ችግር ትምህርት መውሰድ አለባት

90

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2014 /ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዳይሆን ካደረገው የአካታችነት ችግር ትምህርት መውሰድ እንዳለባት በጁባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ረዳት ፕሮፌሰር መከሩ።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ከገባችበት የእርስበርስ ጦርነት ለመውጣት የተለያዩ የሰላም አማራጮችን ተከትላለች።

ከእነዚህም መካከል እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2017 ወደ ሥራ ያስገባችው አገራዊ ምክክር አንዱ ሲሆን ምክክሩም የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም።

ለዚህም ደግሞ ምክክሩ የአካታችነት ችግር መኖሩን ነው የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት።

ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት በደቡብ ሱዳን ጁባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ረዳት ፕሮፌሰር አብርሃም ኮኣ ንዮን ኢትዮጵያም አካታችነት ላይ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባል ይላሉ።   

በደቡብ ሱዳን የተካሄደው ምክክር የጸጥታ ችግር በነበረበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው፤ በምክክሩ የተወሰኑ ሥፍራዎች ሳይካተቱ መቅረቱን ነው የገለጹት።

በዚህም አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ደቡብ ሱዳንም ከእርስበርስ ግጭት ወጥታ ወደ መረጋጋት እንዳትመለስ ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር አካታችነቱ እንዲረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሂደቱን ሕዝባዊ እንዲሆን ንቁ ተሳታፊ በመሆን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።   

በሌላ በኩል የደቡብ ሱዳን በአገራዊ ምክክሩ የተነሱትና በመጨረሻም ለውሳኔ የቀረቡት ምክረ-ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ አለመሆኑም ሌላኛው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጽም የመከሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን ተሞክሮን በደንብ ማጤን አለባት ብለዋል።   

በተጓዳኝም አገራዊ ምክክሩ ተዓማኒና ግልጸኝነት እንዲኖረው የመገናኛ ብዙኃን አጠቃላይ ሂደቱን ሽፋን ሊሰጡት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።  

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ችግሮችን በመፍታት ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ የምትታወቅ መሆኗን አንስተው፤ አገራዊ ምክክሩም ስኬታማ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ኮሚሽኑ አጠቃላይ ሂደቱ ግልጽና ተዓማኒ እንዲሁም አካታች እንዲሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ያህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት በአገራዊ ምክክር የሚመጡ ምክረ-ሃሳቦችን ለመተግበር አምኖ የምክክር ሂደት መጀመሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎቹን በአራት ምዕራፍ ከፍሎ እያከናወነ መሆኑ ይታወሳል።