የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሚካሔዱ የኢኖቬሽንና ምርምር ስራዎችን ለመደገፍ ዝግጁ ነው

74

አዲስ አበባ ግንቦት 04/2014 (ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሚካሔዱ የኢኖቬሽንና ምርምር ስራዎችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን በህብረቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ ገለጹ።

የትምህርት ሚኒስቴር ህብረቱ ያዘጋጀውን እድል አሟጦ ለመጠቀም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት ከወዲሁ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል ብሏል።

የአውሮፓ ህብረትና ትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በምርምር ማዕከላት የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን ለመደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂዷል።

በህብረቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ፡ የአውሮፓ ህብረት በሆራይዘን ፈንድ አማካኝነት ኢትዮጵያን በምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የረጅም ግዜ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው፤ በአገሪቱ የሚካሄዱ የምርምርና የኢኖቬሽን ስራዎችን በመደገፍ ህብረቱ ያለውን አጋርነት በተግባር ለማሳየት ዝግጁ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዛት አንጻር የሚሰሩት የምርምር ስራዎች በቂ አለመሆናቸውን ገልጸው የተሻሉ የምርምር ስራዎች እንዲወጡ ማገዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ህብረቱ ያበረታታል።

ከኢትዮጵያ አልፈው የዓለምን ችግር ይፈታሉ ተብሎ ለታመነባቸው የምርምር ስራዎች ህብረቱ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር፤ ህብረቱ በምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፎች ከሚደግፋቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች።

ለምርምር ስራዎች ተብሎ የሚመደበው የመንግስት በጀት በቂ ባለመሆኑ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ፕሮግራሙን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀምና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ድጋፉ ተግባራዊ የሚሆነው ከአፍሪካ አገራት ተማራማሪዎች ጋር በሚደረግ ውድድር መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ካላት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አኳያ ዕድሉን ለማግኘት አስቻይ ሁኔታዎች አላት ይላሉ።

በዚህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት የበሰለ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የአገሪቱ የልማት አጀንዳዎች ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት በምርምር ዘርፉ ያመቻቸውን እድል ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የምርምር ስራዎች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እንደሚቋረጡ አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ገልጸዋል።

የተካሄዱ የጥናትና የምርምር ስራዎችም እንዲሁ ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ጥረት ቢደረግም በዚሁ ምክንያት ተግባራዊ ሳይደረጉ የሚቀሩበት ሁኔታዎች እንዳሉ አመላክተዋል።

በዚህም በአውሮፓ ህብረት የሚደረገውን ድጋፍ በአዎንታ በመቀበል ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም የሚበቃ የምርምር ስራን ለማከናወንና ያላቸውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም