በቴክኖሎጂ የተደገፈ የደን ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው

203

ግንቦት 04/2014(ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የደን ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ።

ባለሥልጣኑ በአካባቢ ጥበቃና በተፈጥሮ ደን አጠባበቅ ላይ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ የደንን ጠቀሜታ በተገቢው ሁኔታ በማሳወቅ እና ግንዛቤ በመፍጠር መጠበቅ ያስፈልጋል።

የተለያዩ አካባቢዎች ያሏቸውን መልካም ተሞክሮዎች ማጋራት ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ቢሆንም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡

የደን ሃብትን ለመጠበቅ በአካባቢው የሰፈሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

ደንን ለመጠበቅ ኅብረተሰብን ከማስተማርና ከማንቃት በዘለለ ከነባር ደን ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት መዘርጋት ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የደን ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አሰራሩም በደን ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ነገሮችን ቀድሞ ለመተንበይ እና ጉዳቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያግዝ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሀገሪቱ ያለውን የደን ሀብት ለመንከባከብ ደኑ በሚገኝበት አካባቢ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አማራጭ የገቢ ምንጭ ሊፈጠርላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የባለሀብቱን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ አቅም ያላቸው አካላት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል፡፡

የአውራምባ ማኅበረሰብ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ እናነይ ክብረት፤ ተፈጥሮን እና አካባቢ ጥበቃን ከሰው ልጅ ማንነት ጋር በማገናኘት የሚኖር በመሆኑ ተፈጥሮን የመንከባከብ ልምድ ማዳበራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰው ልጅ ተፈጥሮን ካልተንከባከበ መኖር እንደማይችል ገልጸው፤ ሁሉም ተፈጥሮን መንከባከብ የሚያስችል አስተሳሰብ ማጎልበት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም 50ኛ ዓመት ጉባኤ ተሳታፊ እንደምትሆን በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

ጉባኤው ባለፉት 50 ዓመታት የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ የተሰሩ ሥራዎች ያስገኙት ውጤትና የታዩ ጉድለቶች የሚለዩበት እና በቀጣይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚመላከቱበትም ተጠቁሟል ፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥና ብክለት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በዓለም ላይ ለሚከሰቱት የጎርፍ፣ ድርቅና ረሃብ አደጋዎች መንስኤ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም