የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ለታለመላቸው ግብ እንዲበቁ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል

393

ግንቦት 04/2014 (ኢዜአ)  የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ለታለመላቸው ግብ እንዲበቁ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ሲሉ የቶታል ኢነርጂ የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች ተናገሩ።

የቶታል ኢነርጂ የ3ኛ ዙር የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች በአዲስ አበባ የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግበር ተካሂዷል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል "ሀሌታ ቱቶርስ" የተባለ መተግባሪያ በመፍጠር በምርጥ የሥራ ፈጠራ በሚል አሸንፏል።

የፈጠራው ባለቤት እና የሽልማቱ አሸናፊ ናትናኤል ዓለማየሁ የፈጠራ ውድድሮችን ለማበረታት በቂ ገንዘብ መመደብና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎቸን ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።

የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያበረታቱ ተቋማት እና መንግስት ለዘርፉ በቂ ገንዘብ መድበው መንቀሳቀስና መደገፍ አለባቸው ብሏል።

የፈጠራ ውጤቱ "ሀሌታ ቱቶርስ" መተግበሪያ ከ400 በላይ አስጠኚዎችን ማግኘት የሚያስችል ሲሆን በውድድሩ ተሸላሚ አድርጎታል።

የቡና ገለፈትን ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ በመቀየር በምርጥ የንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ ደግሞ ሆሄያት ብርሃኑ ተሸላሚ ሆኗል።

የፈጠራ ውጤቱ በተለይም ለአርሶ አደሮችና በቡና ልማት ላይ ለተሰማሩ አካላት በእጂጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም እንዲህ አይነት የፈጠራ ውጤቶች በብዙ ልፋትና ውጪ የሚሳኩ መሆናቸውን ጠቅሶ የመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የገንዘብም ሆነ ሌሎች ድጋፎች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግሯል።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሰዎችን በገንዘብ ድጋፍ ማድረግና የፈጠራ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት የቴክኖሎጂ ማዕከሎች ቢገነቡ ሲልም ጠይቋል።

የዳይናሞ ቴክኖሎጂ  ማዕከል በመመስረት በምርጥ የሴት ሥራ ፈጠራ ዘርፍ አሽናፊ የሆነችው ምህረት ረዲ ደግሞ ዘርፉ የገንዘብና የማቴሪያን እገዛን ይጠይቃል ብላለች።

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባር ላይ አውሎ ችግር ፈቺ ለማድረግም ከመንግሥት በተጨማሪ የግል ባለሀብቶችና ድርጅቶች ቢደገፉን በማለት ጠይቃለች።

በ3ኛው ዙር የቶታል ኢነርጂ የሥራ ፈጠራ 355 ተወዳዳሪዎች ተሳትፈው በመጨረሻም በየዘርፉ አሸናፊ የሆኑ 3 የፈጠራ ባለሙያዎች የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።

የውድድሩ አሸናፊዎችም እያንዳንዳቸው የ370 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል።

የዚህ ውድድር አሸናፊዎች በቀጣይ ከ32 የአፍሪካ ሀገራት ሶስት አሸናፊዎች ለሚለዩበት የፈጠራ ውድድር ሥራቸውን ይዘው የሚቀርቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም