የውሃ ሀብት ደህንነት ለመጠበቅ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል- ሚኒስቴሩ

164

አዳማ፤ ግንቦት 04/2014(ኢዜአ) የውሃ ሀብት ደህንነት፣ ጥራትና መጠንን ለመጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ሀብቱ ለብክለትና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እንዳይጋለጥና  ደህንነቱን በዘላቂነት እንዲረጋገጥ  በሚቻልበት ዙሪያ በአዳማ ከተማ  ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዴንጋሞ በወቅቱ እንዳሉት፤  በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እያስከተለ ባለው ጉዳት  የውሃ ሀብት ደህንነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

በተለይ የገፀ ምድር የውሃ ሀብት ደህንነት ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ሀብቱ  እንዲቀንስና የመድረቅ አደጋ እየተጋረጠበት ከመሆኑም ባለፈ ከኢንቨስትመንት ተቋማት በሚወጡ ፍሳሾች ጭምር የመበከል ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የከርሰ ምድር ውሃ በተለይ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የ”ፍሎራይድ ኬሚካል” ይዘቱ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለግብርና ግብዓት የሚውሉ ልዩ ልዩ ኬሚካሎች  ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑን አመላክተዋል።

የውሃ ሀብቱን ደህንነት፣ጥራትና መጠን በዘላቂነት ለመጠበቅ  የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ርብርብ  የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት ።

በዚህም በአካባቢ ስነ ምህዳር ጥበቃ፣ በደን ልማት፣የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግር የተጎዳ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ ሆኖ እንዲያገግሙ ማስቻል ላይ የተቀናጀ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ።

በተለይ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን አጠናክሮ  የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት እንዲኖራቸው በዘላቂነት መንከባከብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል አምባሳደሩ።

በዚህም የውሃ ሀብታችንን ከብክለት የፀዳ፣ ሀብቱን ጠብቆ  በማልማትና በማሳደግ ደህንነቱን በዘላቂነት ማስጠበቅ መቻል አለብን ነው ያሉት ።

በተለይ ዘለቄታዊ የውሃ ሀብት ልማትና ኢንቨስትመንት በማከናወን ሀብቱን ደህንነቱ በተረጋገጠ መልኩ በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል የሁሉም  የጋራ ሃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል።

የውሃ ሀብት ደህንነት መጠበቅ፣ ጥራትና መጠን መጨመር  ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ሁሉም አካላት ተገንዝበው የድርሻውን እንዲወጣ ለማነሳሳት የምክክር መድረኩ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በሚኒስቴሩ የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን መሰረተ ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሃይማኖት በለጠ ናቸው ።

በዚህም  የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ርብርብ በየደረጃው በማስፈለጉ የጋራ ዕቅድ  ተዘጋጅቶ በግብዓት ለማዳበርና ወደ ተግባር ለመግባት ነው ብለዋል ።