ለትምህርታችን ትኩረት ሰጥተን የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት እንሰራለን- አዲስ ገቢ ተማሪዎች

90

መቱ ግንቦት 3/2014 (ኢዜአ) "በልዩነታችን  ተከባብረን  አንድነታችንን በመጠበቅ ለትምህርታችን ተኩረት ሰጥተን የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት እንሰራለን" ሲሉ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለፁ።

መቱ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡለትን ከ4ሺ 500በላይ ተማሪዎች በመቱና በበደሌ ካምፓሶቹ እየተቀበለ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንዳሉት አንድነታቸውን ጠብቀው ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት ይሰራሉ።

ከጂማ ዞን የመጣችው  ተማሪ ሐናን ኢሳ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ መግቢያና መመዝገቢያ ወቅት ግራ መጋባት እንደሚገጥማቸው ትሰማ እንደነበር አስታውሷ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ያየችው ከዚህ የተለየና አስደሳች መሆኑን ትናገራለች።

"ከቤተሰብ መለየት ከባደ ነው" ያለችው ተማሪ ሐናን "እዚህ የመጣነው  ለመማር መሆኑን መረዳትና ለዚሁ ዓላማ ጠንክረን በመስራት ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና ለሀገራችን የምንጠቅም ሰዎች ሆነን መውጣት ይኖርብናል" ብላለች።

ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ተማሪዎች የብሔር፣ የባህል፣ የቋንቋ እንዲሁም የኃይማኖት ልዩነቶች እንዳሏቸው ገልጻ ሐናን "በልዩነታችን  ተከባብረን  አንድነታችንን በመጠበቅ ለትምህርታችን ተኩረት ሰጥተን የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት እንሰራለን" ስትል ተናግራለች።

ከደቡብ ክልል ኮንታ ዞን የመጣው ተማሪ ታምራት ታደሰ  በበኩሉ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰቱንና ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ያየበት መሆኑን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የመጣበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጠንክሮ እንደሚሰራ ጠቁሙ  ከዓላማውን ከሚያስቱት ማናቸውም ተግባራትና አመለካከቶች በመጠንቀቅ ለትምህርቱ ብቻ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቋል ።

ጊዜያቸውን ከሚሻሙ አልባሌ ነገሮች ራሳቸውን በመጠበቅና ልዩነቶቻቸውንም በመቻቻልና በመከባበር በመልካም የአብሮነት ዕሴት ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ዜጋ ለመሆን የትምህርታቸውን በአግባቡ እንደሚከታተሉ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡት ደግሞ ተማሪ ኢብራሂም አብደላና ራሔል ብርሃኑ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የጥፋት አጀንዳዎቻቸው ማራመጃ መሳሪያ አድርገው ሊጠቀሙ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ሳይዘናጉ  ትምህርታቸውን  በትኩረት እንደሚከታተሉ አመላክተዋል።

በአቀባበል ስነ ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የመቱ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ፈንታዬ አሰፋ "ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ  ከቤተሰቦቻችሁ ተለይታችሁ ረዥምና አጭር ርቀቶችን አልፋችሁ  የመጣችሁበትን ዋና  ዓላማ  ለማሳካት መትጋት ይኖርባችኋል " ብለዋል ።

"የላኳችውን ቤተሰቦቻችሁን ድካም በምንም ሁኔታ መዘናጋት የለባችሁም " ሲሉም አክለዋል።

ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሌሎች አጀንዳዎችን እያቀረቡላቸው ከአላማቸው ሊያስቷቸው ከሚቀርቧቸው አካላትም ራሳቸውን መጠበቅና በምንም መታለል እንደሌለባቸው መክረዋል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ለታ ዴሬሳ ለተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ሲሉ አቀባበል አድረገውላቸዋል ።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሚያስፈልገው ሁሉ እንደሚያግዛቸውና ብቁ ዜጎች አድርጎ ሊቀርፃቸው መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ተማሪዎችም ባገኙት ዕድል በአግባቡ በመጠቀም እርስ በርሳቸው በመቻቻል፣ በአብሮነት፣ በመተጋገዝ ፣ ፍቅርን መሰረት ባደረገ አንድነት በመገዛት ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም