ታዳጊ ህጻናት በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ሰንቀዋል

75
አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 በዓለም አገሮች የሚኖሩ ህዝቦች እንደ እምነታቸውና ባህላቸው የራሳቸውን የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅተው እንደሚጠቀሙ እሙን ነው። በተለይ የአይሁድ፣ የክርስትና፣ የሂጅራ፣ የቻይና፣ የፋርስና ሌሎችም የዘመን መቁጠሪያዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ኢትዮጵያም የራሷ የዘመን መቁጠሪያ ያላት አገር ናት። የአሮጌው ዓመት የመጨረሻ ነሐሴ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም ወር ድረስ በወጣት ልጃገረዶችና ወንዶች የሚዘወተሩት በአደይ አበባና በለምለም ሳር የሚታጀቡት የቡሄ፣ የአሸንዳ፣ የሶለል፣ የአሸንድዬ፣ የአበባዬ ሆይ ( እንቁጣጣሽ) እና የእንግጫ በዓላት የሚጠቀሱ ናቸው። በአዲስ ዓመት ወንዞች የሚጎሉበት፣ ገበሬው የምርቱን እሼት የሚበሉበት፣ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበት፣ አዲስ ዕቅድና ተስፋ የሚወጠንበት ነው። በተለይም አዲስ ዓመት ሲመጣ ህጻናት የክረምቱ መውጣትን ተከትሎ በአዲስ መንፈስና ተስፋ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡበት በመሆኑ በታላቅ ጉጉት ይጠብቁታል። በዚህ በአዲሱ 2011 ዓመት በጎ ነገሮችን በማሰብ ጠንክረው በመማር ለአገራቸው አስተዋጽኦ ለማበርከት ብሩህ ተስፋ ሰንቀው መነሳታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳጊ ህጻናት ተናግረዋል። ታዳጊ ፍርዶስ ሽፈራው በሰጠችው አስተያየት2011 አዲስ አመትን በትምህርቴ ውጤታማ ለመሆን እሞክራለሁ፤ጎበዝ ተማሪ ለመሆን በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ተዘጋጅቻለሁ ነው ያለችው፡፡ "አዲሱን አመት አዲስ ተስፋ እንዲኖረንና በአሉን ደግሞ በጥሩ መንገድ ከሌላው ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ "ያለችው ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ታዳጊ አይናለም መሸሻ ናት ፡፡ ታዳጊ መስከረም መሳይ በበኩሏ"በአዲስ መንፈስና በአዲስ ተስፋ አዲሱን አመት ለመቀበል እየተዘጋጀን ነው፤ የተሻለ ቦታ ለመድረስ ማጥናትና የተሸለ ውጤት ማስመዝገብ ስላለብኝ ማድረግ ያለብኝን ጥረት ሁሉ አደርጋለሁ" ብላለች፡፡ አሮጌውን ዓመት ለመሰናበትና አዲሱን ዓመት ለመቀበል በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩ ሲሆን 2011 ዓመት " በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር " በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበር ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም