የገበያ ችግሮችን ለመቅረፍ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል

113

ሀዋሳ ግንቦት 3/2014 (ኢዜአ) በገበያ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የንግድ ሥርዓቱንና ተቋማትን ማዘመን እንደሚገባ ምሁራን አመላከቱ ።

“የንግድ ሁኔታንና ተቋማትን ማሻሻል ለተሻለ የኢንቨስትመንት፣ቱሪዝምና ቀጣይነት ያለው ልማት” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ባዘጋጀው ኮንፍረንስ የንግድና ገበያ ሥርዓትን ለማዘመን የሚረዱ እንዲሁም የባንክ አገልግሎትና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ 18 ጥናታዊ ጽሁፎች  እንደሚቀርቡ ተመላክቷል።

ለሁለት ቀን  በሚቆየው ኮንፍራንስ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈሰ ማቲዮስ በኮንፍረንሱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በገበያው ላይ እየገጠመ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመፍትሄ አመላካች ምርምሮች ያስፈልጋሉ።

በኮንፍረንሱ የንግድ ከባቢና ተቋማት በገበያው ሥርዓት ላይ ያላቸው ምቹነት ላይ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች እንደሚሰበሰቡ አመላክተዋል።

ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ፤ ከብድር አሰጣጥና መሰረተ ልማትን ጨምሮ የመረጃ ተደራሽነትና መሰል ችግሮች ለገበያው ሥርዓት ዋነኛ ችግሮች ስለመሆናቸው በጥናትና ምርምር ስራዎች መረጋገጡን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል። 

የንግድ ከባቢና ተቋማት ቁመና ያለመሻሻል የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ከመጉዳቱም በላይ፤የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ አሻራ እያሳረፈ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ሀገሪቱ በ10 አስርመት መሪ ዕቅዷ ውስጥ ያስቀመጠችው 'የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት'ንራዕይ ለማሳካት ከታሰበ የንግድ ሥርዓትን በማሻሻል የንግድ ከባቢንና ተቋማዊ ቁመናን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የንግድ ተቋማት አደረጃጀት ጊዜውን የዋጀ፤ አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች መዘጋጀት ወሳኝ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና ተመራማሪ ዶክተር ወገነ ማርቆስ በበኩላቸው የንግድ ከባቢን ማመቻቸት ከኢንቨስትመንትና ከቱሪዝም እንዲሁም ከአጠቃላይ የዕድገት ምሶሶዎች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ገልጸዋል።

የኦን ላይን ንግድ ሥርዓት መከተል ጊዜንና ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈ የመረጃ እጥረትን በማቃለል ገበያን ለማዘመን እንደሚያስችሉ የተናገሩት  ደግሞ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሀብት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተገኝ ንጉሴ ናቸው።

ምሁሩ ''የአምራች ድርጅቶች የኦን ላይን አገልግሎትና ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ'' በሚል ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፋቸው በአምራቾችና በሸማቾች መካከል የተፈጠረውን የመረጃ ክፍተት መሙላት ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የኦን ላይን ቢዝነስ በፍጥነት እያደገ ቢመጣም፤በኤሌክትሪክና በኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል ደካማነት ዘርፉ እንዳያድግ ተግዳሮቶች እንደሚታዩበት አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም