ብዝኃ ብሔርና ሃይማኖት ጌጥና ዋልታ እንጂ የግጭት መንስዔ ሊሆኑ አይገባም - ምሁራን

125

ሚዛን ፣ ግንቦት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ብዝኃ ብሔርና ሃይማኖት የማህበራዊ መሠረቶቻችን ጌጥና ዋልታ እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንደገለጹት፤ ኅብረ ብሔራዊ ማንነት፣ በአብሮነት፣ በመቻቻልና በመከባበር እሴቶች ላሏት ሀገር የእምነት ልዩነቶች የግጭት መንስኤዎች መሆን አይገባቸውም።

የዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ መምህር ተሾመ ደስታ ኢትዮጵያ ያሏት መልካም እሴቶች ለችግሮች ሳትበገር ፀንታ እንድትቆይ ማድረጉን ገልጸው፤ ለዘመናት የዳበሩትን እነዚህ እሴቶች በወጣቱ ትውልድ ውስጥ እንዲሰርፁ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል ብለዋል።

''በተለይ ብዝሃ ብሔርና ሃይማኖት የማኅበራዊ መሠረቶቻችን ጌጥና ዋልታ ናቸው '' ያሉት መምህር ተሾመ፤ ''ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ የግጭት መንስኤ እንዲሆኑ የሚጥሩ አካላትን በህብረት ማስቆም ይገባል'' ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንድ አካላት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ሲሞክሩ እንደሚታይ ገልጸው፤ ህዝቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን አብሮነት በማጠናከር ሴራቸውን ማምከን ያስፈልጋል  ብለዋል።  

በዩኒቨርስቲው የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር አዳነ ኮርቦ በበኩላቸው ሰዎች ከመጥፎ  ድርጊት እንዲቆጠቡ የሃይማኖት ሕግጋትና አስተምህሮ ያላቸው ሚና የላቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በሚቃረን መልኩ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትና ጥፋት እንደሚያስቆጭና ዳግም እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው ኢትዮጵያውያን ለሰላማችን፣ ለአንድነታችንና ፍጹም ወንድማዊነታችንን ለማስቀጠል እንትጋ ሲሉም ጠይቀዋል።

የግለሰቦች እኩይ ፍላጎትና የጥፋት አዝማሚያ እምነትንና ብሔር እንደማይወክል መምህር አዳነ ገልጸዋል።

ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ያነገቡ ጥቅመኞች ኢትዮጵያ የተመሠረተችበት አለት ጠንካራ በመሆኑ መግቢያ ፍለጋ በዙሪያዋ እያንዧበቡ መሆናቸው ገልጸዋል።

ሠላምን በፀጥታ አካላት ጥረት ብቻ ማረጋገጥ ስለማይቻል ሁላችንም ሰላምና ደህንነቱን ለማስከበር ተባባሪና ተሳታፊ መሆን ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ከጠላት መንጋጋ ለማውጣት ዜጎች በብሄርና በሃይማኖት ሳንከፋፈል  በአንድነት እንቁም ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም