'ኤችአር 6600' እና 'ኤስ 3199' ረቂቅ ሕጎች ባለሥልጣናትን ብቻ እንደሚጎዱ የሚሰነዘረው ሀሳብ የተሳሳተ ነው

112

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 02/2014(ኢዜአ)  “ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች ቢጸድቁ የሚጎዱት መንግሥትና ባለሥልጣናት ብቻ ነው'' የሚለው እሳቤ የተሳሳተ መሆኑን በፍሎሪዳ ግዛት ታምፓ ቤይ ከተማ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተወካይ ሳምራዊት አዱኛ ገለጸች።

ሳምራዊት አዱኛ ዳያስፖራው ረቂቅ ሕጎቹ በኮንግረስና ሴኔቱ እንዳይጸድቁ በተለያዩ አማራጮች ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጻለች።

ትውልደ-ኢትዮጵያዊያኑ በየአካባቢያቸው ያሉ ተመራጮቻቸውን በአካልና በስልክ በማነጋገር፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መልዕክቶችን ቀርጾ በማስተላለፍና ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ሕጎቹ ለድምፅ አሰጣጥ እንዳይቀርቡ በመሥራት ላይ እንደሆኑ ተናግራለች።

ዳያስፖራው ተወካዮቹን ስለ ሕጎቹ እንዲያስረዳ ቅስቀሳ የማድረግና ሕጎቹ የደረሱበትን ደረጃ የተመለከቱ መረጃዎች ልውውጥ በየጊዜው እንደሚደረግም አመልክታለች።

''በሚደረጉ ዘመቻዎችና እንቅስቃሴዎች ዳያስፖራው ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ እንዳይጸድቅ ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛል'' ነው ያለችው ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ የማኅበረሰብ ተወካይ።

በሌላ በኩል “ረቂቅ ሕጎቹ ቢጸድቁ የሚጎዳው መንግሥትንና ባለሥልጣናትን ብቻ ነው'' የሚሉ ሰዎች የሕጎቹን ይዘት በትክክል ያልተረዱ ናቸው ብላለች።

ሕጎቹ ከጸደቁ በቀጥታ ተጎጂ የሚሆኑት የዕለት-ተለት ኑሮ ለማሸነፍ የሚጥሩ ሰዎች መሆናቸውን በማንሳት፤ በሕጎቹ ላይ የተቀመጡ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድሩ ገልጻለች።

ሕጎቹ ቢጸድቁ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርጋቸው የልማት ፕሮግራሞች እንደሚቋረጡና በመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚ በሆነው ማኅበረሰብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግራለች።

አሜሪካ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የምታገኘውን ብድርና የብድር ማራዘሚያ እንዳታገኝ ጫና እንድታሳድር ረቂቅ ሕጉ ምክረ-ሀሳብ እንደሚያቀርብና ይህም በንግድና ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር አመልክታለች።

“ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ጉዳት ለማድረስ የተዘጋጁትን ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ በማሳደግ ለአገሩ የመቆም ግዴታ አለበት” ብላለች።

ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም በአሜሪካ በሚካሄደው የአጋማሽ ዓመት ምርጫ(ሚድ ተርም ኢሌክሽንስ) ምዝገባ በማድረግ የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት የሚሰሩ እጩ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በድምፅ መቅጣት ይኖርባቸዋል ስትልም ተናግራለች።

‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ ለአሜሪካ ኮንግረስ እንዲቀርብ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ መሆኑ ይታወቃል።

ከ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ ለአሜሪካ ሴኔት እንዲቀርብ የተዘጋጀ ነው።

‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’  የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

'ኤስ 3199' ረቂቅ ሕግ ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ማድረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም