በአማራ ክልል በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻው ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የፀጥታ ሃይሎች የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

158

ባህር ዳር፤ ግንቦት 2 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት "በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት" በሚል መሪ መልእክት በህልውና ዘመቻው ተሳትፎ ላደረገው የጸጥታ መዋቅር የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም በዛሬው እለት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጦርነቱ የላቀ ተሳትፎ ላበረከቱ ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት እውቅና እንደሚሰጥ በመርሃ ግብሩ ተመልክቷል።

በህልውና ህግ ማስክበር ዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ የፀጥታ አካላት የማእረግ እድገትና በቀበሌ ደረጃ የላቀ አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላት እውቅና ይሰጣቸዋል።

ከእውቅናው ጎን ለጎን የትግል ሂደቱን የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽን ተከፍቶ ይፋ እንደሚሆን ከመርሃ ግብሩ መገንዘብ ተችሏል።

በእውቅና አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ፣ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በነገው እለትም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በሚገኙበት መሰል ስነ ስርአት እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም