ለኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀው ስልጠና ሥራቸውን በእውቀት በመምራት ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ ተገለጸ

279

ደሴ፤ ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት 2/2014(ኢዜአ) ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የተዘጋጀው ስልጠና ሥራቸውን በእውቀት በመምራት ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገለጸ።

ባንኩ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ወሎ ዞኖች ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና እየሰጠ ነው።

በደብረ ማርቆስ ከተማ በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ የባንኩ የደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ታሪኩ እንደተናገሩት ፤ ስልጠናው ኢንተርፕራይዞች የስራ እንቅስቃሴያቸውን በእውቀትና ክህሎት ለመምራት እገዛ ያደርጋል።

በስልጠናው የሂሳብ አያያዝ፣ የደንበኛ አቀራረብ፣ የገበያ ትስስር፣ የብድር አወሳሰድና አመላለስ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።

ከስልጠናው በኋላም ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

በባንኩ የደሴ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሀብትህ ይመር ከበደ በበኩላቸው፤  ባንኩ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን  በመደገፍ ራሳቸው ተጠቅመው ለሀገርም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን  አቅማቸውን አጎልብተው በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ በመሆን  የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተኩና ብድር  እንዲያገኙ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡

ለስልጠናው ተሳታፊዎች በሊዝ ፋይናንስ የብድር ፖሊሲ፣ በቢዝነስና የሰው ኃይል አስተዳደር፣ በቢዝነስ ፕላንና  በሂሣብ መዝገብ አዘገጃጀት ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ከባንኩ ጋር የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ   በተለያዩ  ስልጠና ማዕከላት  ከትናንት ጀምሮ ተመሳሳይ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን፤ ስልጠናው እስከ ግንቦት 5/2014 እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም