የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራችንን እናጠናክራለን- የምክር ቤት አባላት

94

ሀዋሳ፤ ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) እየተከናወኑ ያሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የክትትልና ቁጥጥር ስራችንን እናጠናክራለን ሲሉ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አባላት አስታወቁ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት 1ኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቅ ተከትሎ ኢዜአ ከአባላቱ ጋር ቆይታ አድርጓል ።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ሮዛሪያ እሸቱ እንደገለጹት በክልሉ ትልቁ የስልጣን ባለቤት ምክር ቤት በመሆኑ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የመከታተል ሃላፊነት አለበት፡፡

"የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ውጤት እንዲያመጡ የክትትልና ቁጥጥር ስራን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

"የምክር ቤቱ አባላት በህዝብ ያገኘነውን ውክልና ተጠቅመን የህዝቡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነት አለብን" ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ሮዛሪያ አክለው ከጉባኤው አስቀድሞ  በምክር ቤቱ አሰራርና ደንብ ላይ ለአጠባላቱ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው ስልጠናው "ሃላፊነታችንን በተገቢው እንድንወጣ  የሚያግዘንን አቅም ፈጥሮልናል" ብለዋል ።

በቀጣይም የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ጭምር  አስፈጻሚውን የመጠየቅ አሰራር እንደሚከተሉ ተናግረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ እየተስተዋሉ ላሉ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትናና በተለያዩ ግብዓቶች ላይ ለሚታየው ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት አስፈጻሚ አካላት መፍትሄ እንዲያበጁ አጽንኦት መሰጠቱን ወይዘሮ ሮዛሪያ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት እንዲወጣ ለማስቻል የአባላቱን አቅም የማጎልበቱ ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው የጠየቁት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል አቶ ወላንሳ ሄንጋሞ ናቸው።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ክልሉ በሀገር ላይ ተደቅኖ የነበረውን የህልውና አደጋ በመመከት ሂደትና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ተግባር ላይ የነበረው ሚና የሚደነቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የአስፈጻሚ አካላትን ስራ ከመከታተልና መቆጣጠር ባለፈ ተቀራረቦና ተደጋግፎ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

ከጉባኤው አስቀድሞ በተሰጣቸው ስልጠና ሰፊ ግንዛቤ መጨበጣቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ መሰረት መንገሻ ናቸው፡፡

ስልጠናውን ተከትሎ በክልሉ ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ላይ ከጉባኤ በፊት ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ያነሱት  ወይዘሮ መሰረት በጥንካሬና በጉድለት የታዩ ችግሮችን በመለየት አቅጣጫ እንዲቀመጥ መደረጉን  ተናግረዋል፡፡

"የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈጻሚ አካላት ላይ የምናደርገውን ክትትልና ቁጥጥር ከማጠናከር ባለፈ  ህብረተሰቡ በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል ስራ እንሰራለንዕ  ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም